ተፈናቃዮችን በዛላቂነት ለማቋቋም ኹሉም አካል ርብርብ እንዲያደርግ ተጠየቀ።

32

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ ከሰው ሠራሽ እና ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር በተያያዘ ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት እና በማቋቋም ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል። ለውይይት የስትራቴጂክ ሰነዱን ያቀረቡት በኮሚሽኑ ቅድመ ማስጠንቂያ እና ምላሽ ባለሙያ ከፍያለው ጎላ ከክልሉ ውጭ እና በክልሉ በተፈጠሩ የተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

ሰነዱ ላይ ውይይት መደረጉ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ችግራቸውን ለመፍታት ከማን ምን ይጠበቃል የሚለውን ባለቤት ለመስጠት እንዲቻል ታስቦ መኾኑንም ተናግረዋል። ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ማቋቋም በኮሚሽኑ ብቻ የሚተገበር ባለመኾኑ ኹሉም አካል በቻለው አቅም ድጋፍ እንዲያደርግ በስትራቴጂ ሰነዱ ተጠቁሟል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እታገኘሁ አደመ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን ወደነበሩበት ለመመለስ የክልሉ መንግሥት እና ሌሎች አካላት በቅንጅት እየሠሩ አንደኾነ ገልጸዋል። ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ዜጎች ተፈናቅለዋል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ ችግሩን የሰሜኑ ጦርነት እና በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዲባባስ አድርጎታል ነው ያሉት።

ለተፈናቃዮቹ የዕለት ደራሽ ድጋፍ ከመስጠት ባለፈ በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሠራ ቢኾንም ከችግሩ ስፋት አንፃር አኹንም የኹሉንም አካላት ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። ከዩኤንዲፒ እና ከኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የተውጣጣ የጥናት ቡድን ተደራጅቶ የሥትራቴጂ ሰነድ እና የሚጠይቀውን የድጋፍ ልክ ለማወቅ እና ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ሲሠራ መቆየቱንም ምክትል ኮሚሽነሯ አስረድተዋል፡፡

በስትራቴጂ ሰነዱ ላይ ውይይት መደረጉ ተጨማሪ ግብዓቶችን ለማግኘት እንዲኹም በተገኙ ሃሳቦች መነሻ በማድረግ ሃብት ለማሠባሠብ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል። ተፈናቃዮችን ኹል ጊዜ በድጋፍ ማኖር ስለማይቻል ዘላቂ መፍትሄ መስጠት እና ራሳቸውን እንዲችሉ ማቋቋም ወሳኝ መኾኑንም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር ረጂ ድርጅቶች፣ ማኅበረሰቡ፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎችም ድጋፋቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል። አኹንም ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

በመድረኩ የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አጋር አካላት ተወካዮች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገር በቅብብሎሽ የምትቀጥል እንደመኾኗ ለተተኪ ተውልድ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል።
Next articleሰላምን ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ በዳባት ከተማ የተሐድሶ ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ ሠልጣኞች ተናገሩ።