የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅንን ውጤታማ ለማድረግ ቁልፍ ተግባር አድርጎ እንደሚሠራ የሰሜን ሸዋ ዞን አስታወቀ።

27

ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን የ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል። በንቅናቄ መድረኩ የወረዳ የዞን አመራሮች እና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
የመምሪያው ኀላፊ ወይዘሮ ፀዳለ ሰሙንጉስ በ2016 በዞኑ ከ275 ሺህ በላይ አባወራዎች የጤና መድኅን አባል መኾናቸውን ተናግረዋል።

የሞረት እና ጅሩ፣ ሀገረማርያም ከሰም፣ ሲያደብርና ዋዩ ወረዳዎች እና የሸዋሮቢት ከተማ አሥተዳደር በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ወረዳዎች መኾናቸውን አንስተዋል። በ2017 በጀት ዓመት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በመሥራት ከ420 ሺህ በላይ የጤና መድኅን አባላት ለማፍራት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ውጤታማ ለማድረግ አመራሩ ቁልፍ ተግባር በማድረግ ይሰራበታል ብለዋል። የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አባል የማፍራት፣ የመድኃኒት አቅርቦቱን ማሻሻል፣ ለታካሚዎች ምቹ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ የማድረግ እና ገቢ የመሰብሰብ አቅምን የማሳደግ ሥራዎች በትኩረት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየቅጥር ማስታወቂያ !
Next articleበጎ ፈቃደኞች ለኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት እየተወጡት ያለው ሚና የሚደነቅ መኾኑን ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ.ር) ገለጹ።