“ሀገራዊ ምክክሩ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተግባብተን እንድናልፍ የሚያደርግ ነው” ዶክተር ደሴ ጥላሁን

37

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከዓመታት በፊት ሀገራዊ ዕድል አልፎታል፡፡ በበቂ እና በብቁ ሁኔታ አልተወከልኩበትም ባለው ሕግ ሲተዳደር ቆይቷል። ፖለቲከኞች በፈጠሩት ትርክት ያልወሰደውን እዳ ከፍሏል። ታዲያ ለእነዚህ ሥርዓታዊ እና መዋቅራዊ ችግሮች ሥርዓታዊ እና መዋቅራዊ መፍትሔዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ከ1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የተነሱ ፖለቲከኞች ሲጎዱት ኖረዋል፡፡ ከመነሻቸው በትርክት፣ በሂደታቸው እና በመዳረሻቸው ደግሞ በሥርዓት በደል አብዝተውበታል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አቋቁማ እየመከረች ነው፡፡ ሀገራዊ ምክክሩ ጥል እና ጥላቻ የሚወድቅበት፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዕውነታቸውን ይዘው የሚቀርቡበት፣ መክረው ዘክረው የጋራ የኾነ ዕውነት ይዘው የሚወጡበት፣ የራሳቸውን ዕውነት አስረድተው የሌሎችንም ዕውነት የሚረዱበት፣ ትናንት ላጎበጧቸው ችግሮች መፍትሔ የሚዘይዱበት፣ ለነገ ጉዟቸው የጋራ መንገድ የሚቀይሱበት፣ የሚስማሙበትን እና የሚያምኑበትን ሕግ የሚያረቅቁበት፣ ቁርሾ እና መገፋፋትን ጥለው አንድነትን እና ፍቅርን የሚያጠነክሩበት ነው፡፡

ታዲያ በዚህ ምክክር በንቃት እና በብቃት መሳትፍ እልፍ ጉዳዮችን ያተርፋል፡፡ አለመሳተፍ ደግሞ የትናንቱን ስህተት ያስደግማል፡፡ ከዘመናት መካከል የተገኘውን ዕድል ያስመልጣል፡፡ ትውልድ ላይ የሚጫን ስህተትም ያሠራል፡፡ የአማራ ክልል በ1980ዎቹ በረቀቀው ሕገ መንግሥት በንቃት እና በብቃት ተሳትፎ ቢኾን ኖሮ በሥርዓት እና በመዋቅር የተደገፉ በደሎች ገፈት ቀማሽ ባልኾነ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ያለፈው ዕድል ከአንድ ትውልድ ዕድሜ በላይ ለሚኾን ዘመን ዋጋ አስከፍሎታል፡፡

አሁን ግን ስህተት የሚያርምበት፣ ሲከፍለው የኖረውን ዋጋ የሚጥልበት ዕድል አግኝቷል፡፡ ዕድሉን ከተጠቀመበት መልካም ካልተጠቀመበት ግን ተጨማሪ ትውልድ የሚጎዳ፣ ምን አልባትም ዳግም የማይገኝ ዕድል ያመክናል፡፡ የሕግ ምሁሩ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) በዓለም ተሞክሮም በታሪክም ሂደት ሀገራዊ ምክክር የሚካሄደው መሠረታዊ በሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች በሊህቃን፣ በፖለቲከኞች፣ በማኅበረሰብ መካከል አለመግባባት ሲፈጠር እና የሀገረ መንግሥት ግንባታው ገና ያላለቀ ሲኾን ነው ይላሉ፡፡

ሀገረ መንግሥት ግንባታው ያልተጠናቀቀ ሲኾን የሚያጋጥሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት፣ ሀገረ መንግሥትን ለማስቀጠል፣ በሕዝብ እና በመንግሥት ቅቡልነት ያለው መሠረት እንዲኖር ለማድረግ ይካሄዳል ነው የሚሉት፡፡ ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ፋይዳው ከፍተኛ ነው የሚሉት ምሁሩ ስለ ምን ቢባል ሀገረ መንግሥት ግንባታው ያልተጠናቀቀ በመኾኑ፣ በልሂቃን፣ በፖለቲከኞች፣ በኅብረተሰቡ ልዩነቶች ስላሉ ነው ይላሉ፡፡

ስኬታማ እና ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር እንዳደረጉ ሀገራት ሁሉ እኛም ያለመግባባት እና የልዩነት ምንጮች ምንድን ናቸው? የሚሉትን ማኅበረሰቡ እንዲለያቸው በማድረግ በእነርሱ ላይ በመወያየት፣ በመግባባት፣ በመስማማት የልዩነት ምንጮችን መፍታት ይገባናል ነው የሚሉት፡፡ ሀገራዊ ምክክር የልዩነት ምንጮችን በመፍታት ዘላቂነት ያለው ሰላምን በማረጋገጥ ሀገራዊ መግባባት እንዲኖር ያስችላል፡፡

ሕዝብ የሚያነሳቸው እና መፈታት የሚገባቸው ጥያቄዎች አሉ የሚሉት ምሁሩ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ መፈታት አለባቸው ከምንላቸው ጥያቄዎች መካከል በሕገ መንግሥት ላይ መግባባት፣ በሕገ መንግሥት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ቋጭቶ ማለፍ ነው ይላሉ፡፡ ሌላው ጉዳይ በተሳሳተ መንገድ ሲነዛ የኖረው ትርክት ነው፡፡ በተሳሳተ መንገድ ሲነገር የኖረው ትርክት አንደኛው ያለ መግባባት ምንጭ ኾኖ መቆየቱን ነው ያነሱት፡፡

እንደ ሀገር አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ ደግሞ መግባባት አለብን ነው የሚሉት፡፡ሀገራዊ ምክክር የማንግባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ብሎ ይለያል፡፡ መሠረታዊ ጉዳዮች ደግሞ አካታች በኾነ መንገድ የሚነሱት ከማኅበረሰቡ ነው ይላሉ፡፡ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ጋር ሲነጻጸር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአካታችነት መርሕ ለየት ያለ ባሕሪ አለው፤ ለምን ከተባለ በጣም ሰፊ የማኅበረሰብ ክፍል እንዲሳተፍ ነው የሚፈልገው ነው የሚሉት፡፡

“ሀገራዊ ምክክሩ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተግባብተን እንድናልፍ የሚያደርግ ነው” ይላሉ፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ወሳኝ የሚባለው የምክክር አጀንዳዎችን መለየት ነው የሚሉት ምሁሩ የምክክር አጀንዳዎች ደግሞ የሚለዩት ከማኅበረሰቡ ነው፣ እንደ ማኅበረሰብ የሚነሱ ጥያቄዎችን በጋራ ተወያይቶ ወሳኝ የሚባሉትን አንጥሮ የማውጣት ሂደት ነው፣ ወሳኙ ጉዳይም እዚህ ላይ ነው ይላሉ፡፡

ያልተጠናቀቀ ሀገረ መንግሥት በመኖሩ ምክንያት ለግጭት እየተዳረግን ስለኾነ እና ጥያቄዎችም ስላሉን ሀገራዊ ጉዳዮች ተነስተው፣ ውይይት ተደርጎባቸው ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር ብንግባባ ሌሎች ሀገራት እንዳደረጉት ሁሉ እኛም ችግሮቻችን ልንሻገር እንችላለን ብለዋል፡፡ የሀገራዊ ምክክር ሂደት አካታች፣ ሰላማዊ፣ በንግግር እና በውይይት የሚካሄድ አሸናፊ እና ተሸናፊ የሌለበት ነው ይላሉ፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደት መሳተፍ ለአማራ ክልል ሕዝብ ትልቅ ፋይዳ አለው ነው የሚሉት፡፡

ሀገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲኾን ሁለት ጉልህ ጉዳይ ይነሳል የሚሉት ምሁሩ የመጀመሪያው ፖለቲካዊ ዝግጁነት፣ ቁርጠኝነት፣ በትክክለኛ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ፣ ከጀርባ ምንም ዓይነት አጀንዳ የሌለው፣ ችግርን ፈትቶ ሀገርን ለማሻገር ያለመ መኾኑ ነው ይላሉ፡፡ ሁለተኛው ጉልህ ጉዳይ ደግሞ አሳታፊነት፣ አካታችነትን መሠረት ያደረገ፣ ሁሉም አጀንዳቸውን አዋጥተው፣ በምክክሩ ተሳትፈው የመጨረሻ ውጤት ላይ መድረስ የሚችሉበት መኾኑ ነው ብለዋል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ማገዝ እና መተባበር ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡ ሀገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን ይዞ ከመላው ኢትዮጵያውያን ፊት ቀርቦ ምክክር የሚደረግበት በመኾኑ አጀንዳ መለየት፣ መሳተፍ መሠረታዊ ነው ይላሉ፡፡ ሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ሰላማዊ እንዲኾን ሁሉም ኀላፊነት አለበት የሚሉት የሕግ ምሁሩ መንግሥት፣ ማኀበረሰቡ እና የፖለቲካ ኀይሎች ኀላፊነት አለባቸው ነው የሚሉት፡፡

ውጤታማ ሀገራዊ ምክክር ካደረግን ውጤታማ ከኾኑ ሀገራት ተርታ እንሠለፋለን ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችን በኢትዮጵያ ማዕቀፍ የሚፈቱ በመኾናቸው፣ ትልልቅ አጀንዳዎችም ስላሉን፣ አጀንዳዎቹ ለሀገራዊ ምክክር መቅረብ የሚችሉ በመኾናቸው ጥያቄዎቹ እልባት እንዲያገኙ መሥራት ብልህነት ነው ባይ ናቸው፡፡

መሠረታዊ ጥያቄዎች ያሉበት የአማራ ሕዝብ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በንቃት በመሳተፍ ውጤታማ እንዲኾን ማድረግ አለበት ነው ያሉት፡፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሲዋቀር ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው በአዋጁ የተቀመጡት ያሉት ምሁሩ የመጀመሪያው መሠረታዊ የኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት የኾኑ አጀንዳዎችን መለየት፣ ሁለተኛ ውይይቱ አካታች እንዲኾን ማድረግ፣ ሦስተኛው ደግሞ ውይይቱን በገለልተኝነት የሚያስፈጽም አካል መኖር አለበት የሚሉ ናቸው ይላሉ፡፡

በአዋጁ ላይ እንደተቀመጠው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከየትኛውም የፖለቲካ ወገን ሳይኾን፣ በኢትዮጵያውያን የሚመራ የኢትዮጵያ ተቋም ነው ብለውታል፡፡ ተቋማዊ ነጻነቱን ጠብቆ የተደራጀ ተቋም መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ገለልተኝነቱ ጥያቄ ውስጥ አይገባም ነው የሚሉት፡፡ ውይይት የሚያድነን መፍትሔ ነው በማለት የታጠቁ ኀይሎችም አጀንዳቸውን ለኮሚሽኑ በማቅረብ መወያየት፣ መከራከር እና የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ ይችላሉ ነው ያሉት፡፡

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ችግር በውይይት መፍታት ይቻላል ብሎ የሚያምን መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ችግሮቻችን በውይይት ፈትተን ነገ እና ከነገ ወዲያ ታሪክ የሚያስታወሰን መኾን አለብንም ይላሉ፡፡ የአማራ ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አሉ የሚሉት ምሁሩ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በአግባቡ አለመሳተፍ ሌላ ስህተት መሥራት ነው ብለዋል፡፡

ጥያቄዎችን ይዘን ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ልንወያይባቸው ይገባል፣ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በንቃት መሳተፍ፣ አጀንዳዎችን ማሠባሠብ፣ አጀንዳዎች ነጥረው እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ያለፈውን ሂደት አሁን መድገም አያስፈልግም፣ ጥቅሞቻችን የሚከበሩት በአንዲት ሀገር ነው ብለዋል፡፡ ይሄ ታሪካዊ አጋጣሚ ሊያልፍ አይገባም ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ለድርጅቶቹ ሃብት የመፍጠር ነጻነትን የሰጠ ነው።
Next articleተፈናቃዮችን በዛላቂነት ለማቋቋም የሚያግዝ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ምክክር እየተካሄደ ነው።