የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ለድርጅቶቹ ሃብት የመፍጠር ነጻነትን የሰጠ ነው።

22

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ላይ ከሕግ አውጭ አካላት እና ከምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢዎች ጋር ውይይት አድርጓል። የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባ እና ክትትል ቡድን መሪ አለልኝ አጉማስ የአማራ ክልል መንግሥት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት መመዝገቢያ እና ማሥተዳደሪያ አዋጅ ቁጥር 194/2004 ዓ.ም ከ10 ዓመት በላይ በሥራ ላይ መቆየቱን አንስተዋል።

በዚህ ጊዜ ውስጥ በተፈጠረው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጥ ምክንያት ተግባራትን ለማከናወን ባለመቻሉ አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል። የአዋጁ መሻሻል የመደራጀት መብትን ተግባራዊ ለማድረግ፤ የመንግሥትን አሠራር በግልጽነት፣ በተጠያቂነት እና በአሳታፊነት ለማከናወን፣ የነቃ እና በነጻነት የተደራጀ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እንዲቻል ዓላማ ያደረገ ነው።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በክልሉ ልማት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው ሚና እንዲጎለብት፣ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ ሥራቸውን በሕግ መሠረት መሥራታቸውን ለመቆጣጠር እንዲቻል አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል። በኅብረተሰቡ ዘንድ የበጎ አድራጎት እና የበጎ ፈቃደኝነት ባሕል እንዲዳብር፣ በሥራ ላይ የነበረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና የማኅበራት አዋጅ ቁጥር 194/2004 የነበሩበትን ክፍተቶች ለመሸፈን የሚያስችል ማሻሻያ ማድረግ እና ሌሎች ምክንያቶች ለአዋጁ መሻሻል እንደምክንያት ተወስዷል።

አዋጁ በቢሮው የተመዘገቡ እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ ተፈፃሚ ይኾናል። ይሁን እንጅ በሃይማኖት ተቋማት፣ በእድር፣ በእቁብ እና መሰል ባሕላዊ ሥብሥቦች፣ በባለሥልጣኑ የተመዘገቡ ድርጅቶች፤ በባለሥልጣኑ የተመዘገቡ እና በክልሉ የተመዘገቡ ድርጅቶች በሚፈጥሯቸው ኅብረቶች ወይም የኅብረቶች ኅብረት እና በሌላ ሕግ መሠረት በተቋቋሙ ተቋማት ላይ አዋጁ ተፈፃሚ እንደማይኾን ተነስቷል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ሀናን አብዱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባ በፍትሕ ቢሮ በኩል ይካሄዳል፤ ከሕግ ውጭ ኾነው ከተገኙ ደግሞ ፈቃዳቸውን እስከ መሰረዝ ኀላፊነትን የያዘ ረቂቅ አዋጅ ነው። አዋጁ ድርጅቶች ሃብት እንዲፈጥሩ ነጻነትን የሰጠ፣ ለሚሠሩት ሥራ ደግሞ የተጠያቂነት ሥርዓት የዘረጋ ነው። ረቂቅ አዋጁ ላይ የሕግ ምሁራን ተሳትፈውበታል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብት አሥተዳደር እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ አበራ ፈንታሁን እንዳሉት ደግሞ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኀፊነታቸውን እንዲወጡ የምክር ቤት አባላት ክትትል እና ቁጥጥር ላይ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተዘነጋው የጤና ችግር!
Next article“ሀገራዊ ምክክሩ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተግባብተን እንድናልፍ የሚያደርግ ነው” ዶክተር ደሴ ጥላሁን