
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ የ2017 ዓ.ም ጤና መድኅን የነባር አባላትን እድሳት እና የአዲስ አባላት ምዝገባ ንቅናቄ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል። መድረኩ “እንደ አቅሜ አዋጣለሁ፤ እንደ ህመሜ እታከማለሁ” የሚል መሪ መልዕክትም ነበረው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ዓለም አሰፋ እንዳሉት በ2016 ዓ.ም ከ48 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ተደራሽ ኾኗል። ለዚህም ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ ለሕክምና ወጭ ተደርጓል። ለአንድ አባልም እስከ 133 ሺህ ብር ለሕክምና ወጭ መደረጉን ነው መምሪያ ኀላፊዋ ያስታወሱት። ይህም የጤና መድኅንን ፋይዳ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ብለዋል።
በ2017 ዓ.ም ደግሞ 63 ሺህ 713 ወገኖችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው የከተማዋ ጤና መምሪያ ኀላፊዋ ያስታወቁት። በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን በመታቀፍ በነፃ ታክሞ ጤንነትን የማረጋገጥ ዕድል ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊዋ ዓለም አሰፋ የመክፈል አቅም የሌላቸውን ነዋሪዎች በመለየት እና በጎ ፍቃደኛ ድርጅቶች፣ ባለሃብቶች እና ግለሰቦች እንዲሸፍኑላቸው ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግም ገልጸዋል።
ስለኾነም የጤና መድኅን አባል በመኾን ያተርፉበታል እንጂ አይከስሩበትም ብለዋል። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የ2017 በጀት ዓመት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክን ሲያስጀምሩ ዘርፉ የመረዳዳት ባሕልን በማጎልበት አቅመ ደካሞችን የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በገንዘብ እጥረት ለመታከም የተቸገሩ ወገኖችን በመታደግ ረገድ የጤና መድኅን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት። በትንሽ መዋጮም ሕይዎትን መታደግ አስችሏል ብለዋል። ለአሚኮ አስተያየታቸውን የሰጡ የጤና መድኅን ተጠቃሚ እንዳሉት ከከተማ እስከ ገጠር ያሉ ወገኖች የጤና መድኅን ተሳታፊ እየኾኑ ነው። ነገር ግን አገልግሎት ሰጭዎቹ “መድኃኒት የለንም” በማለት እና አሠራራቸውን ግልጽ ባለማድረግ አባሉ እየተጉላላ ይገኛል ነው ያሉት።
ሌላዋ አስተያዬት ሰጭ “ትንሽ አውጥተን በፈለግንበት ሰዓት እና ቀን በነጻ እንድንታከም አድርጎናል ብለዋል። የጤና መድኅን ባይኖር ኑሮ በርካታ አቅመ ደካሞች ይቸገሩ እንደነበርም ነው የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!