
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ ዛሬ በአዲስ አበባ የተገነቡ እና በመገንባት ላይ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተናል ነው ያሉት።
በጉብኝታቸው የኮሪደር፣ የአካባቢ ሥነ ምህዳር ጥበቃ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ ማኅበራዊ ተቋማት፣ የፒያሳ እና ካዛንቺስ መልሶ ማልማት እና ለተነሽዎች ሁሉን አሟልተው የተገነቡ መንደሮችን መመልከታቸውን ነው የተናገሩት። በከተማዋ የተጠናቀቁ እና እየተፋጠኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ፈጠራ እና ፍጥነትን አስተሳስረው እየተከናወኑ መኾኑንም አይተናል ነው ያሉት።
በከተማዋ ለልማት ተነሺዎች የተገነቡ ቤቶች፣ የተቀናጁ የማኅበራዊ ተቋማት እና የመሠረተ ልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን የቀድሞ ሕይወት ከመለወጥ ባለፈ የብልጽግና ፓርቲን ሰው ተኮርነት በተጨባጭ ያረጋገጡ ተግባራት ናቸው ብለዋል። የኮሪደር ልማት ከተሞችን የማብቃት ሥራ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሞች ሲቆረቆሩ በታሪክ አጋጣሚ እንጂ በዕቅድ አልነበረም ነው ያሉት። ይሄም ለኑሮ፣ ለቢዝነስ እና ለአገልግሎት ምቹ እንዳይኾኑ አድርጓቸዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የዘመናትን የከተማነት ፈተና የሚፈታ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሪደር ልማቱ መኖሪያን፣ የሥራ ቦታን፣ ቢዝነስን፣ ቅርስን፣ ማኅበራዊ ትሥሥርን፣ እንቅስቃሴን፣ ጤናን፣ ጽዳትን እና መዝናኛን በጥቅሉ የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻልን አማክሎ እየተገነባ ነው ብለዋል።
የነገዋን አዲስ አበባ ለማየት እና ለመኖር የምታጓጓ ናት፤ ተመሳሳይ ሥራ ለጀመሩ የክልል ከተሞች ምሳሌ እና ሞዴልም ኾናለች ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!