
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ከተሞችን ለኑሮ ምቹ በማድረግ የሕዝቡን ሕይወት በሚቀይሩ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ እየሠራ ነው ሲሉ የፓርቲው ሥራ አሥፈፃሚ አባል እና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል። የብልጽግና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በተለያዩ ጉዳዮች እየተወያየ ይገኛል።
በዚህ ውይይት የፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ትግበራን እየገመገመ እንደሚገኝ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈፃሚ አባል እና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል። በተለይ ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲኾኑ፣ ዲጂታላይዜሽን እንዲስፋፋ፣ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲዘምን፣ አረንጓዴ ሽፋናቸው እንዲያድግ በተቀመጠው መስረት ትልልቅ ሥራዎች መሠራታቸውን ሥራ አሥፈፃሚው ገምግሟል ብለዋል።
በዚህም ፍሳሽ፣ ውኃ፣ መብራት እና ቴሎኮም ደረጃቸውም እንዲጠብቁ፣ አቅም የሌላቸው ሰዎችን ምገባ እና የቤት ተጠቃሚ እንዲኾኑ የሚያስችሉ ሥራዎች በፓርቲው አቅጣጫ መሰረት ተተግብረዋል ነው ያሉት። በእነዚህ ትግበራዎችም አዲስ አበባ ቀዳሚ ትኩረት ተሰጥቷታል ያሉት ከንቲባ አዳነች የአዲስ አበባ ትኩረት ማግኘት የሀገር ገፅታ መቀየር መቻል እና ለሌሎች ከተሞች ተምሳሌት መኾኑን በሚያሳይ መልኩ ተሠርቷል ሲሉ አብራርተዋል።
በዚህም አዲስ አበባ የአረንጓዴ ሽፋን ከ2.8 በመቶ ወደ 20 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። አዲስ አበባን ለነዋሪዎች የተመቸች ለማድረግ 265 ሺህ ቤቶች በግሉ ዘርፍ እና በመንግሥት መገንባት መቻሉን አንስተዋል። በከተሞች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብዙ እንደሚቀር የተብራራ ሲኾን በዋናነት አገልግሎት ሰጭው ባለሙያ ከተቀየረው ኹኔታ ጋር ራስን አለማያያዝ እና ለብልሹ አሠራር መጋለጥ ትልቁ ችግር መኹኑ ተገምግመዋል ተብሏል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!