ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ እንዲመሩ ለማድረግ መንግሥት ቁርጠኛ መኾኑ ተገለጸ፡፡

21

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ያስችላል ያለውን የስትራቴጂ ጥናት ለባለድርሻ አካላት አቅርቦ አወያይቷል፡፡ በአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ የጥናቱ ዓላማ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋ ምክንያቶች ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ይህንን ሥራ ለመሥራትም ስትራቴጂ አዘጋጅቶ መፈጸም የሚያስችል መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ሦስት አማራጮች መጠናታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት ቀያቸው መልሶ ማቋቋም፣ ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ ፍላጎት የሌላቸውን ደግሞ ተጠልለው ባሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ በመደገፍ ማቋቋም እና በሌላ አካባቢ በማስፈር ማቋቋም መኾናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ጥናቱ ሥራዎች ለመሥራት አቅጣጫዎችን፣ የሚጋጥሙ ችግሮችን ከእነመፍትሄዎቻቸው የሚያመላክት መኾኑን ነው ያነሱት፡፡

ተፈናቃዮችን ወደነበሩበት ክልል መልሶ ለማቋቋም የነበሩባቸው ክልሎች ሰላም መኾኑን ማረጋገጥ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ ተናቃዮች ወደ ነበሩበት አካባቢ ተመልሰው መቋቋማቸው የበለጠ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እታገኘሁ አደመ ችግሩን በዘላቂነት መፈታት እንዲቻል ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ስትራቴጅያዊ ሰነዱ ለውይይት መቅረቡን ገልጸዋል፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንደሚወያዩበትም አንስተዋል፡፡

በክልሉ ውስጥ እና ከክልሉ ውጭ የተፈናቀሉ ወገኖች መኖራቸውን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሯ በክልሉ ውስጥ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል፤ ነገር ግን ድጋፍ እና ዘላቂ መፍትሔ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡ ከአማራ ክልል ውጪ ተፈናቅለው የመጡ ወገኖችንም በዘላቂነት መፍትሔ ለመስጠት በጥናት ሰነድ ማዘጋጀት እና ስትራቴጂ መንደፍ ማስፈለጉን ነው የተናገሩት፡፡ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ከሚቀበለው ክልል መሪዎች፣ ከበይነ መንግሥታት ቢሮ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት እንደሚኸንም አመላክተዋል፡፡

በጥናት የተዘጋጀው ስትራቴጂ ዓላማ በምክክር እና በውይይት በሚደረግ መግባባት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው፣ ሰላማቸው እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ ከተረጂነት ኑሮ እንዲወጡ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ሥራውም በሂደት ይፈጸማል ነው ያሉት፡፡ ተፈናቃዮች እስኪመለሱ ድረስ ባሉበት ድጋፍ እንደሚደረግም አስታውቋል፡፡ ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ አማካሪ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) የውይይት መድረኩ በተዘጋጀው ስትራቴጂው ላይ ለባለድርሻ አካላት ግልጽነት ለመፍጠር የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ስትራቴጂው እንዲዘጋጅ እና መመሪያ ኾኖ እንዲያገለግል ለማድረግ ማሰቡ ዜጎች ወደቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ቁርጠኛ መኾኑን ያመላክታል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከሚሠራው ሥራ በተጓዳኝ የክልሉ መንግሥት ከክልሎች እና ከበይነ መንግሥት ጋር በመወያየት ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ ሢሠራ መቆየቱን ነው የገለጹት፡፡ በሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች በመመካከር ይፈታሉ ነው ያሉት፡፡ የችግሩን ሥረ መሠረት አውቆ እልባት ለመስጠት በመንግሥት ደረጃ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ የተፈናቃይ መረጃን ከክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን መውሰድ እንደሚገባ የተናገሩት አማካሪው ሃብት ለማሰባሰብ ሲባል የሚገለጹ ቁጥሮች ተገቢ አለመኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ አጋር አካላትም የመንግሥትን ጉድለት በመሙላት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ የተዘጋጀው ስትራቴጂ ስኬታማ እንዲኾን ባለድርሻ አካላት በመደጋገፍ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢኮኖሚ እና በሰላም ዘርፍ የላቀ አበርክቶ የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ተሸለሙ።
Next articleከ60 ሺህ በላይ ወገኖችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።