በኢኮኖሚ እና በሰላም ዘርፍ የላቀ አበርክቶ የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ተሸለሙ።

21

አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኢኮኖሚ እና በሰላም ዘርፍ የላቀ ተግባር ያከናወኑ እና አርዓያነት ያላቸውን ግለሰብ እና ተቋም ለመሸለም በሚል ዕጩዎች ተለይተው ድምፅ ሲሰጥ ቆይቶ ዛሬ ለአሸናፊዎቹ ሽልማት ተበርክቷል። “ሰላም ከሌለ ቢዝነስ የለም” የሚል መሪ መልዕክት አንግቦ የሚንቀሳቀሰው አንቴክስ ቴክስታይል ፒኤልሲ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢኮኖሚ እና በሰላም ዘርፍ ለተመረጡ ሁለት ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለእያንዳንዳቸው 10 ሚሊዮን ብር ሸልሟል።

ዕጩዎቹ በተለያዩ የመምረጫ መስፈርቶች ለውድድር የቀረቡ ሲኾኑ ብርቱ ፉክክርም ሲያደርጉ ቆይተዋል። ለአሸናፊዎቹ የዋንጫ ሽልማት የተዘጋጀ ሲኾን ዋንጫዎቹ ለእጩዎች ሁለት እና ለአሸናፊዎቹ ደግሞ አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ሙሉ በሙሉ ከብር የተሠሩ መኾናቸው ተገልጿል።

በዚህም በሰላም ዘርፍ የጋሞ አባቶች አሸናፊ ሲኾኑ በቢዝነስ ዘርፍ ደግሞ ኢንጂነር ቢጃይ ናይከር አሸናፊ ኾነው ሽልማታቸውን ወስደዋል። የጋሞ አባቶች ሁሉም ለሰላም እንዲሠራ ጠይቀዋል። ኢንጅነር በጃይም በተወካዩ አማካኝነት መልሶ ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች እንደሚሸልመው ይፋ አድርጓል።

ዓላማው በመላው ሀገሪቱ ለሰላም የተጉ፣ ሥራ ፈጥረው ብዙኀንን ያበረቱ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን መሸለም ሲኾን በሰላም እና በኢኮኖሚ ዘርፍ አምስት እጩዎች ተመርጠው የመጨረሻው ፉክክር ሲደረግ መቆየቱ ይታወሳል።

አንቴክስ ቴክስታይል ፒኤልሲ የተባለ የቻይና ተቋም በዓይነቱ ልዩ የኾነውን የመጀመሪያውን “የምርጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፈጻሚዎች ሽልማት” መርሐ ግብርን ከበሻቱ ቶለማርያም መልቲሚዲያ ጋር በጋራ እንዳዘጋጁት ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ድልነሳ መንግሥቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ብልጽግና ፓርቲ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በጥራት በመፈጸም ሀገራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው” አብርሃም በላይ (ዶ.ር)
Next articleተፈናቃዮች ወደቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ እንዲመሩ ለማድረግ መንግሥት ቁርጠኛ መኾኑ ተገለጸ፡፡