“ብልጽግና ፓርቲ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በጥራት በመፈጸም ሀገራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው” አብርሃም በላይ (ዶ.ር)

25

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ.ር) ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት በሜጋ ፕሮጀክቶች የሠራውን ሥራ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም በኢትዮጵያዊያን ትብብር የተጀመረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት የተጀመሩ የኀይል ማመንጫና የመስኖ ሜጋ ፕሮጀክቶች በጥራትና በታለመላቸው ጊዜ ተገንብተው ባለመጠናቀቃቸው በሕዝብ ዘንድ ቅሬታ ሲነሳ መቆየቱን ተናግረዋል። ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ሀገራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ነው ያሉት። ለአብነትም የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህያው ምሥክር ነው ብለዋል።

በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ግንባታው ቆሞ የነበረው የኮይሻ የኀይል ማመንጫ ፕሮጀክት አሁን ላይ መንግሥት በወሰደው ቁርጠኝነት 69 በመቶ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል። የግንባታ ሂደቱ በመጓተቱ ረጅም ዓመታትን የስቆጠረው የመገጭ የመስኖ ፕሮጀክትም ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እየተገነባ መኾኑንም ተናግረዋል። የመስኖ ፕሮጀክቶቹ በተቋራጮች የአቅም ውስንነት፣ በበጀት እጥረት እና በፕሮጀክት የአመራር ሥርዓት ችግር ምክንያት ሲጓተቱ መቆየታቸውንም አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ወደ ማምረት የሚገቡ የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል
Next articleበኢኮኖሚ እና በሰላም ዘርፍ የላቀ አበርክቶ የነበራቸው ኢትዮጵያውያን ተሸለሙ።