
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች እና በልዩ ልዩ የፓርቲ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር የቆየው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ ከውይይቶቹ በመነሳት የተለያዩ ውሳኔዎች በማሳለፍ አቅጣጫዎችን ሰጥቷል። በውይይቱ ከተዳሰሱ ጉዳዮች አንዱ የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪው ነው፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች ለመፍታት እና ተወዳዳሪ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል። በአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ወደ 60 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው አንድ ጊዜ እየሞቀ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየቀዘቀዘ መቆየቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ መጀመሪያ የእሳቤ እና የአሠራር ለውጥ በማድረግ መጀመር በማስፈለጉ በለውጡ ማግስት ትኩረት የተሰጠው የእሳቤ ለውጥ ላይ ነበር ብለዋል። አምራች ኢንዱስትሪዎች ለውጭ ገበያ ብቻ ሳይኾን ለሀገር ውስጥ ገበያ ማምረት እንዲችሉ ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ተወዳዳሪነታቸው እንዲያድግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አንስተዋል። በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ላይ ማሻሻያ በመደረጉ ከለውጡ በፊት ወደ 46 በመቶ ወርዶ የነበረው የማምረት አቅም አሁን ላይ ወደ 60 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ነው የገለጹት።
ከለውጡ በፊት 30 በመቶ የነበረው የአምራች ኢንዱስትሪው የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ አሁን ላይ 40 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል። የአምራች ኢንዱስትሪው የውጭ ባለሃብቶች ፍሰትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። ወደ ማምረት የሚገቡ የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ቁጥርም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት እና ለመዋቅራዊ ሽግግር መሳለጥ ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት መቻሉንም ገልጸዋል። በሥራ ዕድል ፈጠራም ትልቅ ለውጥ ታይቷል ብለዋል፡፡
ጥሩ እድገት እየታየበት ያለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሀገራዊ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦው ከፍ ብሎ እንዲቀጥል የተቋማት ቅንጅት እና ትብብርን የሚጠይቅ መኾኑን አንስተዋል። እንቅፋት የኾኑ ችግሮችን ለማስተካከል ሁሉም ትኩረት እንዲሰጥ እና የተሻሉ የቅንጅት ሥራዎች እንዲሠሩ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አቅጣጫ መስጠቱንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አብነት እስከዚያ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!