
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት በተለያዩ ረቂቅ ሕጎች ላይ ከሕግ አመንጪ አካላት እና ከምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ጋር ውይይት አድርጓል። ከቀረቡት ሕጎች ውስጥ የአሥተዳደር ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ አንዱ ነው።
የአሥተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ በብዙ ሀገራት ተግባራዊ የተደረገ ሕግ ቢኾንም በኢትዮጵያ ከ1960 ጀምሮ ከረቂቅነት ያለፈ አልነበረም። ይሁን እንጅ በሀገሪቱ በ2013 ዓ.ም የአሥተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕጉ እንዲወጣ ተደርጓል። ብዙ ክልሎችም ሕጉን አውጥተዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) እንዳሉት የአሥተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕጉ የሚወጡት መመሪያዎች ከረቂቁ ጀምሮ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ፣ ሕግን የተከተሉ፣ ፍትሐዊነትን የሚያረጋግጡ፣ ከሕግ ጋር የማይጋጩ እና የዜጎችን መብት የማያጣብቡ መኾናቸውን ለማረጋገጥ አላማ ያደረገ ነው። አስፈጻሚ አካላት ውሳኔዎችን በምን ያህል ጊዜ እንደሚሰጡ፣ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ቅሬታ ካለ ደግሞ ቅሬታ ሰሚ በማደራጀት በተነሱ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የመስጠት ግዴታን ያስቀምጣል። በቅሬታ ውሳኔዎች ላይ ቅሬታ አቅራቢው የማይረካ ከሆነ ደግሞ መመሪያዎች በፍርድ ቤት የሚከለሱበት መደበኛ ሥርዓት ተፈጥሯል።
የሚወጡ መመሪያዎችን በድረ ገጽ እና በተለያዩ አማራጮች ማኅበረሰቡ እንዲያውቃቸው ይደረጋል ብለዋል። ከዚህ በፊት የወጡ የአስፈጻሚ አካላት መመሪያዎች ደግሞ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በፍትሕ ቢሮ እንዲመዘገቡ ይደረጋል ብለዋል። በቀጣይም ከሕዝብ ግብዓቶችን በመሰብሰብ ለምክር ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅ ይደረጋል። ለሕጉ ተፈጻሚነት ምክር ቤቱ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ጎሽም እንዳሉት አዋጁ በመንግሥት አሠራር እና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግልፅነትን፣ ተጠያቂነትን፣ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ ያግዛል። የአሥተዳደር ሕጉ በሕግ መሰረት ተግባራትን ለመሥራት፣ ብልሹ አሰራርን ለመከላከል፣ አሥተዳደራዊ ፍትሕ ለማረጋገጥ አላማ ያደረገ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!