“ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን ምጣኔ ሃብት የገነባች ሀገር ኾናለች” የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር)

18

አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) ባለፉት ዓመታት የተሠሩ ሥራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአማካይ 7 ነጥብ 2 በመቶ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ከምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን ምጣኔ ሃብት የገነባች ሀገር መኾኗን ገልጸዋል።

በተለይም በማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ እና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል። በሪፎርሙ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ኢትዮጵያን በዓለም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ካስመዘገቡ ሀገራት ተርታ ማሰለፍ መቻሉን ነው የገለጹት። ከዚህ ቀደም የነበሩትን የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደኾነም አንስተዋል።

በዚህም በማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ እና በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም በሌሎች የኢኮኖሚ አመላካች ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ መኾኑን ጠቅሰዋል። የገቢ መጠንን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ እድገት እና መሻሻል ማሳየት የተቻለበት አጋጣሚ መፈጠሩን የተናገሩት ሚኒስትሯ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ትርፋማነት እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።

በመስኖ ሥራ በተለይም በበጋ መስኖ ልማት በመሠረተ ልማት ግንባታ አመርቂ የሚባል ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል። የተጀመረው ሥራ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በገንዘብ ፖሊሲም ከዚህ በፊት የነበረውን ጉድለት መሙላት ያስቻሉ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።

ዘጋቢ:- ቤቴል መኮንን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያ ገበያ በሚፈልገው መንገድ የተቃኜው የክህሎት ልማት ሥራ ለውጥ አምጥቷል” ሙፈሪያት ካሚል
Next article“የአሥተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕጉ የዜጎችን መብት የሚያስከብር እና ፍትሐዊነትን የሚያረጋግጥ ነው” የአማራ ክልል ምክር ቤት