
ደሴ: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡበ ወሎ ዞን የሚገኙ ወረዳዎች ባሕል እና እሴታቸውን እንዲያስተዋውቁ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የዞኑ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል። በመምሪያው አዘጋጅነት ለሦስት ቀናት የሚቆየው 16ኛው ዞን ዓቀፍ የባሕል እና ኪነ ጥበብ ዓውደ ርዕይ በደሴ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
በዓውደ ርዕዩ ላይ የ16 ወረዳ የባሕል ቡድን አባላት ቱባ ባሕላቸውን በማስተዋወቅ እየተሳተፉ ነው። የባሕል ቡድን አባላቱ ጭፈራዎችን፣ የባሕል አልባሳት እና ቲያትርን እያስተዋወቁ ነው። የፕሮግራሙ መዘጋጀት በዞኑ ያሉ ባሕል እና እሴቶችን ለማወቅ እንዳስቻላቸውም ተሳታፊዎች ገልጸዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አስያ ኢሳ ዞኑ በርካታ ባሕላዊ ሃብቶች እንዳሉት ተናግረዋል። ይህ ዓውደ ርዕይም ወረዳዎች ባሕል እና እሴታቸውን እንዲያስተዋውቁ ለማድረግ የተዘጋጀ መኾኑን አንስተዋል።
ፌስቲቫሉ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሳይካሄድ መቆየቱን ያነሱት ኀላፊዋ የፕሮግራሙ መዘጋጀት ዞኑ ያለውን የባሕል እና እሴት ለታዳሚያን ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመላክተዋል።
በዓውደ ርዕዩ ላይ ባሕሉን ለታዳሚዎች በተሻለ መልኩ ያስተዋወቀ አንድ የባሕል ቡድን ጥር 05/2017 ዓ.ም በጎንደር ከተማ በሚካሄደው ክልላዊ ፌስቲቫል ላይ ዞኑን በመወከል የሚሳተፍ ይኾናል ተብሏል።
ዘጋቢ፡- ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!