በበጋ መስኖ ልማት የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳይኖር እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

9

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የበጋ መስኖ ልማት እየተካሄደ ነው። አርሶ አደሮች የመስኖ ልማት ስኬታማ እንዲኾን የግብዓት አቅርቦት እንዲቀርብላቸው ይጠይቃሉ። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮም የመስኖ ልማቱ የተሻለ እንዲኾን የግብዓት አቅርቦት እያሰራጨ መኾኑን ገልጿል።

አርሶ አደር ዘነበ ማሬ በደቡብ ጎንደር ዞን በፎገራ ወረዳ አፋፍ ችት ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ በዚህ ዓመት የመስኖ ስንዴ ለማልማት እየሠሩ መኾኑን ነግረውናል። ለመስኖ ስንዴ ሥራው የውኃ መሳቢያ ሞተር ከፎገራ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ እጥረት እንዳለ ነው የተናገሩት። እጥረቱን ለመፍታት ከሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ባልተገባ ዋጋ ለመግዛት እንደተገደዱም አስረድተዋል። እጥረቱ እንዲፈታላቸውም ጠይቀዋል። የመስኖ ልማት ሥራን ውጤታማ በማድረግ ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡

ቢሮው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የመስኖ ልማት ሥራን በትኩረት እንደሚሠራ ነው የገለጸው። በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ በ2017 ዓ.ም ከ250 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በመስኖ ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

የተለያዩ ግብዓቶች እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ወደ ታች በማድረስ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ነው የገለጹት። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም የስንዴ ልማትን በስፋት እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። የምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እንዳይኖር እየተሠራ መኾኑን ነው ዳይሬክተሯ የተናገሩት፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 3ሺህ 482 ኩንታል የምርጥ ዘር ስንዴ መሰራጨቱንም ገልጸዋል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ በአንዳንድ አካባቢዎች እጥረት ሲፈጠር የማዳበሪያ ክምችት ካለባቸው ቦታዎች በማንሳት እጥረቱ ወዳለባቸው አካባቢዎች በማዛወር ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በየአካባቢው ያለው የጸጥታ ስጋት አስፈላጊ ግብዓቶችን በወቅቱ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ ችግር እንደኾነባቸውም ነው የገለጹት፡፡

ቴክኖሎጅን ለመጠቀም በዓመቱ ወደ 5 ሺህ የውኃ መሳቢያ ሞተር ለማሰራጨት ታቅዶ 2 ሺህ 291 የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ተደራሽ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን በክልሉ የመስኖ ልማት ባለባቸው አካባቢዎች 29 ሺህ 870 የውኃ መሳቢያ ሞተሮች እንዳሉም አስገንዝበዋል፡፡ አርሶ አደሮች የዝናብ ወቅትን ጠብቆ ከማምረት ልማድ በመላቀቅ የመስኖ ልማት ሥራን በመጠቀም በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ቢሮው በየዘርፉ ካሉ ባለሙያዎች ጋር እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮች ለሕገወጥ ግብይት እና አግባብ ላልኾነ ወጭ እንዳይዳረጉ ግብዓቶችን በሕጋዊ መንገድ በመግዛት እና በመጠቀም ምርት እና ምርታማነትን እንዲያሳድጉም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአልማ 55 ቢሊዮን ብር ሃብት በማሠባሠብ አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ አስታወቀ።
Next articleበዳንግላ ወረዳ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የታጠቁ ቡድኖች መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ገቡ።