
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከአምስቱ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ምሰሶዎች መካከል የኢንዱስትሪው ዘርፍ አንዱ ነው፡፡ በለውጡ ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ውስጥ ሊኖረው የሚገባውን ድርሻ ለማሳደግ፣ በሥራ ላይ ባለው ስትራቴጂ እና ፖሊሲ አቅጣጫዎች ያልተፈቱ ክፍተቶችን መሙላት የሚያስችል ፖሊሲ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
ፖሊሲው የዘርፉን የመልማት አቅም እና መልካም አጋጣሚዎች አሟጦ ለመጠቀም እና ከዘርፉ ተለዋዋጭ ባህሪያት ጋር የሚመጡ የምርት ሥርዓት ሁኔታዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ነው። የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ባለፉት የለውጥ ዓመታት የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች ለመፍታት እና ተወዳዳሪ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች ለውጭ ገበያ ብቻ ሳይኾን ለሀገር ውስጥ ገበያ ማምረት እንዲችሉ ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ተወዳዳሪነታቸው እንዲያድግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አንስተዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ላይ ማሻሻያ መደረጉን ያነሱት ሚኒስትሩ ከለውጡ በፊት ወደ 46 በመቶ ወርዶ የነበረው የማምረት አቅም አሁን ላይ ወደ 60 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል፡፡ የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከፍ ማለቱን ተከትሎ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ የራሱን አዎንታዊ ሚና እያበረከተ መኾኑን አንስተዋል።
ከለውጡ በፊት 30 በመቶ የነበረው የአምራች ኢንዱስትሪው የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ አሁን ላይ 40 በመቶ ማድረስ መቻሉንም ገልጸዋል። ከዚህ ቀደም የነበረው ድርሻ ዝቅተኛ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ አሁን ላይ ከፍተኛ ለውጥ የተመዘገበበት መኾኑን አስረድተዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪው የውጭ ባለሀብቶች ፍሰትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው ወደ ማምረት የሚገቡ የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። በዓመት በዘርፉ ለዜጎች የሥራ እድል የመፍጠር አቅምም 156 ሺህ በላይ መድረሱን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!