“ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የበጎ አድራጊ ድርጅቶች ድጋፍ ያስፈልጋል” የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን

39

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚያስችሉ ስትራቴጂ ላይ ከአጋር አካላት ጋር ዐውደ ጥናት አድርጓል። የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሰርካዲስ አታሌ በሀገሪቱ እና በክልሉ በተከሰተው ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ዜጎች ከአካባቢያቸው እርቀው በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች እንደሚገኙ ገልጸዋል።

90 በመቶው በማኅበረሰቡ ውስጥ፤ 10 በመቶው ደግሞ በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። ባልተመቻቸ ኹኔታ ስለሚኖሩም ሰብዓዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ድጋፍ እንደሚፈልጉም ነው የገለጹት። የተፈናቀሉ ዜጎችን ዓለም አቀፍ ድንጋጌን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በዘላቂነት ለማቋቋም ታቅዶ ጥናቱ መዘጋጀቱንም ምክትል ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።

መልሶ ማቋቋሙም በተለያዩ አማራጮች እንደሚፈጸም የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሯ የመንግሥት አካላት እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ድጋፍ አስፈላጊነትንም አንስተዋል። የሚደረገው ድጋፍም እንደሚሰጠው የምላሽ አማራጭ እና የአካባቢው ጸጋ የሚወሰን ይኾናል። በዘላቂነት የማቋቋም ሥራውን ለመደገፍ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ሚናቸው ትልቅ ነው ብለዋል።

የርእሰ መሥተዳድሩ ተወካይ መስፍን አበጀ (ዶ.ር) በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት በማኅበራዊ ችግሮች በተከሰተው ቀውስ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ይገኛሉ ብለዋል። ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋም በተዘጋጀው ስትራተጂ ላይ ለመምከር እና የጋራ ሃሳብ ለመያዝ የተዘጋጀ መድረክ መኾኑንም ገልጸዋል።

መንግሥት ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ልማት፣ በዴሞክራሲ እና ሰላም ግንባታ እንዲሁም በሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ላይ በትብብር እና በቅንጅት እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ለአስቸኳይ ዘላቂ መልሶ ማቋቋም እና ሰብዓዊ እርዳታ ውጤታማ የትብብር አቅጣጫዎችን እንደሚከተሉም ተናግረዋል።

ለተግባራዊነቱም ስትራቴጅ በመንደፍ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በትብብር እና በቅንጅት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በአማራ ክልል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሀገር በቀል እና የውጭ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ልማት፣ በሰላም፣ በዴሞክራሲ ግንባታ እና ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ እየሠሩ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

የክልሉ መንግሥትም ላደረጉት አስተዋጽኦ ያመሠግናል ብለዋል። የዐውደ ጥናቱ ዓላማም ይህንኑ ምክክር እና መደጋገፍ የሚያጠናክር እንደሚኾን ይጠበቃል። ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካል ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አድርገዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የፍትሕ ተቋማት ሚና ጉልህ ነው።
Next article“የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 60 በመቶ ደርሷል” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል