የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የፍትሕ ተቋማት ሚና ጉልህ ነው።

21

ደባርቅ: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን የደባርቅ ወረዳ የዳኝነት እና ፍትሕ ተቋማት የጋራ ዕቅድ ትውውቅ እና ግምገማ ተካሂዷል። የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የፍትሕ ተቋማት ሚና ጉልህ ነው። ፍትሕን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሂደትም የአጋር ተቋማትን ትብብር ይጠይቃል። የዳኝኘት እና ፍትሕ ተቋማት የምክክር መድረክ የፍትሕ አሰጣጥ ሂደቱን የተሳለጠ እና ተደራሽ እንደሚያደርገውም ተመላክቷል።

የደባርቅ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መገናኛ ሞላ ተቋማቱ ነጻነታቸውን ጠብቀው እንዲሠሩ ለማስቻል የተደረገው የአሠራር ለውጥ እና የጋራ መድረክ መዘጋጀቱ ወሳኝነት አለው ብለዋል። በቀጣይ የፍትሕ ሥርዓቱን ግልጽ፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት እና የተሳለጠ ለማድረግ ዐቅደው እየተንቀሳቀሱ መኾኑንም ገልጸዋል።

የደባርቅ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት የወንጀል ምርመራ ክፍል ኀላፊ ኢንስፔክተር ሊቁ ችሎት የፖሊስ ሥራ ወንጀል እንዳይፈጸም ቀድሞ መከላከል፣ ከተፈጸመ በኋላ ደግሞ ወንጀለኛውን ለሕግ ማቅረብ መኾኑን ተናግረዋል። በተናጠል በሚሠራበት ጊዜ ክፍተቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ ነው ያሉት።
በጋራ ተቀናጅቶ በመሥራት ችግሮችን ማጥበብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። የተገልጋይን እንግልት በመቀነስ የተሳለጠ የፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት ከአጋር ተቋማት ጋር ዐቅደው እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል።

የደባርቅ ወረዳ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የሕጻናት መብት ደህንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ እንዳልካቸው ዋጋው ከፍትሕ ተቋማቱ ጋር በጋራ መሥራት መቻሉ የሴቶችን እና የሕጻናትን ተጋላጭነት ለመቀነስ እና ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል።

ተጋላጭ የኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሚያጋጥሙበት ጊዜም ሚስጥራቸው ተጠብቆ ፍትሕ እና ሕጋዊ ከለላ ለማግኘት የሚችሉበትን ኹኔታ ለመፍጠር አቅደው እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። የጋራ መድረኩ ተግባራትን ለማዘመን እና ሚስጥራዊነቱን ለመጠበቅ ትኩረት ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

የሰሜን ጎንደር ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኀላፊ ኢንስፔክተር አበበ አዳነ የፍትሕ ተቋማትን አጋርነት በሚጠይቅ የትብብር ሥራዎች ላይ የተቋማቱን የጋራ መርሕ መሠረት ያደረገ የዕቅድ ትውውቅ እና ግምገማ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article380 ቢሊየን ብር ገቢ መሠብሠቡን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሡ ገለጹ፡፡
Next article“ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የበጎ አድራጊ ድርጅቶች ድጋፍ ያስፈልጋል” የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን