
ባሕር ዳር: ታኅሳስ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት አምስት ወራት 380 ቢሊየን ብር ገቢ መሠብሠቡን የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ገልጸዋል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የገቢ አሠባሠብ አፈጻጸምን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም በሀገር ደረጃ የተያዙ የልማት ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ዋነኛ አቅም ተደርጎ የሚወሰደው የሀገር ውስጥ ገቢን ማሻሻል እና ማሳደግ ነው ብለዋል። የሀገር ውስጥ ገቢን ማሻሻል የሕዝብ የልማት ፍላጎትን ደረጃ በደረጃ የሚመልሱ መሠረተ ልማቶችን መገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡ በገቢ አሠባሠብ ሂደት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የገቢ አቅምን ማሻሻል የሚያስችሉ መሠረታዊ ለውጦች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል እና አገልግሎት አሰጣጡን ማሳለጥ የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ አሠራሮችን መዘርጋት መቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው ማሻሻያዎቹ በገቢ አሠባሠብ ሂደቱ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም የፌደራል ገቢ 176 ቢሊየን ብር እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሯ አሁን ላይ በአምስት ወር ብቻ 380 ቢሊየን ብር ገቢ መሠብሠቡን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ሊደግፍ የሚችል እና አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ እንዲኖር የገቢ አሠባሠብ ሂደት ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ሊደግፍ የሚችል የሀገር ውስጥ የፋይናንስ አቅም መገንባቱንም አመላክተዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!