ሕዝቡን በማኅበረሰብ ጤና መድኅን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።

25

ደብረ ብርሃን: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ በቀለ ገብሬ ባለፈው በጀት ዓመት ከ25 ሺህ በላይ እማወራዎችን እና አባወራዎችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል። ይህም ከታቀደው አንጻር 82 በመቶ አፈጻጸም እንዳለው ነው ያስረዱት።

በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ ከ32 ሺህ በላይ እማወራ እና አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷል ነው ያሉት። የተያዘውን ግብ ለማሳካት ሰፋፊ የንቅናቄ ሥራዎችን ለማከናወን የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት። የሕክምና አገልግሎት አሰጣጡን ጥራት ያለው እና ተደራሽ ማድረግ ዕቅዱ እንዲሳካ ከሚከናወኑት ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት አዳዲስ የሕክምና አገልግሎቶች ይሰጣል ያሉት አቶ በቀለ ከእነዚህ መካከል የካንሰር ምርመራ እና ሕክምና መጀመሩን ጠቅሰዋል። በሂደቱም ለጋሽ ድርጅቶች ትልቅ ድጋፍ እያደረጉ መኾኑን መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል። ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ችግሮች ይስተዋላሉ ያሉት ደግሞ የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ናቸው።

የተሠበሠበውን ገንዘብ ፈጥኖ ገቢ ያለማድረግ፣ ያልተሠበሠበ ገንዘብን እንደተሠበሠበ አድርጎ ሪፖርት የማድረግ ክፍተቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል። ችግሮችን በማስተካከል የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር በትኩረት መሥራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት። የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ የ2016 በጀት ዓመት በዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አካላት ዕውቅና የሚሰጥበትን እና የ2017 በጀት ዓመት የመክፈል አቅምን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እያካሄደ ነው።

በመድረኩም የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸትን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሥራ ኀላፊዎች እና የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የደሴ ዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ።
Next article380 ቢሊየን ብር ገቢ መሠብሠቡን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሡ ገለጹ፡፡