በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የደሴ ዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ።

44

ደሴ: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከወራት በፊት የተመረቀው የደሴ ዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ በክፍለ ከተሞች ባሉት ማዕከላት ለማኅበረሰቡ ዳቦ ማቅረብ ጀምሯል። በፋብሪካው የሥራ ዕድል የተፈጠረለት ወጣት ሰይድ ጁሀር ከዚህ በፊት ሥራ ስላልነበረው ያሳለፈውን ችግር አስታውሶ አሁን ላይ በተፈጠረለት የሥራ ዕድል የሕሊና ርካታ አግኝቻለሁ ይላል።

ከተመረቅሁበት የትምህርት ዘርፍ ጋር ተያያዥነት ያለው የሥራ ዕድል ተፈጥሮልኝ ሥራዬን በአግባቡ እየተወጣሁ ነው ያለችን ሌላኛዋ የሥራ ዕድል የተፈጠረላት ወጣት መቅደስ አጥላባቸው ሙያዬን በማዳበር ራሴን ለመለወጥ ተዘጋጅቻሁ ነው ያለችው። የደሴ ዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን መኮንን ፋብሪካው በቀን 300 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም እንዳለው ገልጸው በዛሬው ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ከ5 ሺህ በላይ ዳቦ አቅርቧል ነው ያሉት።

በቀጣይም በከተማዋ በሚገኙ በአምስቱም ክፍለ ከተሞች ከ30 በላይ ማዕከላትን በማቋቋም ዱቄት እና ዳቦ የሚያሰራጭ ይሆናል ነው ያሉት። ዳቦውን ከፋብሪካው በወጣበት ዋጋ በሰባት ብር ሒሳብ ለተጠቃሚዎች እንዲቀርብ እየተደረገ ነው ብለዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ከተማ አሥተዳደሩ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በመመደብ የሰው ኀይል እና ግብአትን በማሟላት ዱቄት እና ዳቦ በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረቡ ሥራ በሙሉ አቅም ተጀምሯል ብለዋል።

ፋብሪካው በተሟላ ኹኔታ ሥራ እንዳይጀምር እንቅፋት የነበሩት የጄኔሬተር እና የመብራት ችግሮች መፈታታቸውን ተናግረዋል። የፋብሪካው ሥራ መጀመር የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ያሉት ከንቲባው ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ዘጋቢ ፦ አንተነህ ፀጋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የቡግና ዕውነት ከነዋሪዎቹ አንደበት”
Next articleሕዝቡን በማኅበረሰብ ጤና መድኅን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።