“የቡግና ዕውነት ከነዋሪዎቹ አንደበት”

61

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ ረሃብ አለ ወይ? ሰዎችስ ለከፋ ጉዳት ተዳርገዋልን? ችግሩስ እንዴት ተፈጠረ? ከመቼ ጀምሮስ ተፈጠረ? ደጋጎቹ እናቶች ተርበዋልን? ሕጻናቱስ ተርበዋል ወይ? ባለፉት ጊዜት ተፈጥሮ በሚያመጣው ፈተና እና ሰዎች ከራሳቸው ባሕሪ በሚያመነጩት ግጭት አያሌ ወገኖች ለችግር ሲዳረጉ ቆይተዋል፡፡ ገሚሶቹ ራበን ብለው እጃቸውን ዘርግተዋል፡፡ ገሚሶቹ ተቸግረው ከሚወዷት ቀየ ወጥተው ተሰደዋል፡፡ ከሞቀ ቤታቸው ተለይተው በመጠለያ ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ ሕጻናት ተጠምተዋል፡፡ አረጋውያን በማምሻ ዕድሜያቸው ተጎሳቁለዋል፡፡ እናቶች ለልጆቻቸው የምናጎርሰው አጣን ብለው እርዳታ ጠይቀዋል፡፡

ዛሬም ድረስ በመጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ወገኖች ሞልተዋል፡፡ ከዛሬ ነገ እንመለሳለን እያሉ ለዓመታት ቤታቸውን የሚናፍቁም ብዙዎች ናቸው፡፡ በተፈጥሮ አደጋ እና በሠው ሰራሽ ችግሮች የተጠሙትን ለማጠጣት፣ የተራቡትን ለማጉረስ፣ የታረዙትን ለማልበስ፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉትን ወደቀያቸው ለመመለስ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ያም ኾኖ ዛሬም ድረስ እጃቸውን ለእርዳታ የዘረጉ ብዙዎች ናቸው፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በተፈጠረ የተፈጥሮ እና የሰው ሠራሽ ችግር ምክንያት ነዋሪዎች የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው፣ በአካባቢው የሚራቡ ብዙዎች እንደኾኑ ሲነገር ቆይቷል፡፡ የችግሩ ጥልቀት ምን ያክል ነው? “ውኃን ከጥሩ፣ እውነትን ከሥሩ” እንዲሉ አበው አሚኮ ከቡግና ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ ለደኅንነታቸው ሲባል የነዋሪዎቹን ስም አንጠቅስም፡፡

የቡግና ችግር የሚጀምረው ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ነው ይላሉ ታሪክ ነጋሪያችን፡፡ ለወትሮው ለድርቅ፣ ለበረዶ እና ለሌሎች ችግሮች የሚጋለጠው የቡግና ወረዳ ሕዝብ በሰሜኑ ጦርነት ብዙ ነገር አጥቷል ነው የሚሉት፡፡ የጦርነቱ ጠባሳ ለውሥብሥብ ችግር ዳርጎናል፤ ዘንድሮ ደግሞ የዘራነው ፍሬ ባለመስጠቱ በችግር ውስጥ ቆይተናል ነው ያሉት፡፡ በተፈጠረው ችግር ምክንያት እናቶች እና ሕጻናት እየተጎዱ ነው ብለዋል፡፡

ወቅቱ እንደ ልብ መንቀሳቀስ የማይቻልበት በመኾኑ ርቆ ሄዶ ሠርቶ ለመብላትም አስቸጋሪ ኾኖብን ነው የከረምነው ነው ያሉት፡፡ “እኛ የምንለው ተረስተናል ነው፣ ችግራችሁ ምንድን ነው ብሎ የጠየቀን፣ ጥያቄዎቻችንም የመለሰልን የለም” ይላሉ፡፡ ድርቅ አለብን፣ የውኃ ችግር አለ፣ የጤና ችግር አለብን፣ ልጆቻችንም እየተማሩ አይደለም፤ ብዙ ችግሮች ያሉበት ወረዳ ነው ብለዋል፡፡

“የሚያዝንልን አጥተናል፣ የቡግናን ሕዝብ ችግር የሚረዳ የለም፣ ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነት ስናምሰለስል እናድራለን እንጂ የሚያስብልን የለም” ነው የሚሉት፡፡ የጥያቄያቸው መልስ መዘግየቱን፣ ተስፋ በማጣት ደረጃ ላይ ደርሰው መቆየታቸውንም አንስተዋል፡፡ የሰብዓዊ ድጋፍ የጠየቅነው ዘንድሮ አይደለም፣ ባለፈው ዓመት ነው፣ ረሃብ ጊዜ አይሰጥም፣ ነገር ግን በቶሎ ምላሽ አልተሰጠንም ነው ያሉት፡፡ “ድርቁ የጀመረው ዘንድሮ ሳይኾን ባለፈው ዓመት ነው፤ አሁን ላይ አዝመራ የሚባል ነገር የለንም፡፡ አልቅሰን የምንነግረው አካል አጥተን ነው የከረምነው፡፡ በሀዘን ነው የተቀመጥነው” ብለዋል፡፡

ቡግና የምግብ ችግር ብቻ ሳይኾን የውኃ ችግርም ያለበት ነው ይላሉ፡፡ ከረጅም ጊዜ ጥያቄ በኋላ ከሰሞኑ የሕጻናት አልሚ ምግብ መጥቷል፡፡ ጅማሮው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የቡግናን ሕዝብ ከችግር የሚያወጣ ድጋፍ አልመጣም ነው ያሉት፡፡ በብዛት የሚመጣ ከኾነ እና ለሁሉም ተጎጂ የሚደርስ ከኾነ ጥሩ ነው፡፡ ያ ካልኾነ ግን በረሃብ የሚሞት ይኖራል ብለዋል፡፡ የምግብ እርዳታ ብቻ ሳይኾን የመድኃኒት አቅርቦትም እንሻለን፤ መንግሥት እና ረጂ ድርጅቶችም እንዲደርሱልን እንጠይቃለን ነው ያሉት፡፡

ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ የዘንድው ችግር በዕድሜያችን አይተነው አናውቅም ይላሉ፡፡ መሬቱ ምንም አይነት ሰብል አላሳየንም ነው የሚሉት፡፡ በዚህ ምክንያት እናቶች እና ሕጻናት ችግር ላይ ናቸው ይላሉ፡፡ በጸጥታው ችግር ምክንያት የምንፈልገው የግብርና ግብዓት ሳይደርስልን ነው የከረምነው፡፡ ችግሩ በስፋት የተከሰተው ከሐምሌ ጀምሮ ነው ይላሉ፡፡

ከሰሞኑ ግን የተለያዩ ረጂ ድርጅቶች እና መንግሥት ድጋፍ አቅርቧል፡፡ ለተጎጂዎች ባይደርስም ድጋፉ እየተራገፈ ነው፡፡ ባየነው ነገር ተስፋ እያደረግን ነው፡፡ ተጨማሪ ካልመጣ ግን የመጣው ብቻ በቂ የሚኾን አይመስለንም ነው ያሉት፡፡ አሁን የተጀመረው ነገር ጥሩ ነው ተስፋ ሰጥቶናል፤ ከከረመው ችግር እና ካለው ሰፊ ጉዳት አንጻር ግን አይበቃም ነው የሚሉት፡፡ የተለየ ችግር ነው የገጠመን፡፡ ከባድ ነው፡፡ ተሎ ሊደረስልን ይገባል ነው ያሉት፡፡

አንድ እንጀራ ለሦስት እና ለአራት እየበላን ነው የከረምን ይላሉ፡፡ መንግሥት ችግራችንን አይቶ እንዲደርስልን፤ ረጂ ድርጅቶችም በችግር ውስጥ ላለው ሕዝብ እንዲደርሱለት እንጠይቃለን ብለዋል፡፡ የቡግና ወረዳ አሥተዳዳሪ ጌታዬ ካሳው እንዳሉት በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያት ረሃብ ተፈጥሯል፡፡ ችግሩ በሕጻናት፣ በእናቶች እና በአረጋውያን ላይ የከፋ ነው ብለዋል፡፡ የጉዳት መጠኑን በግብርና ባለሙያዎች እና በጤና ባለሙያዎች ማረጋገጣቸውንም ነው የተናገሩት፡፡ አካባቢው ከወትሮውም ለድርቅ ተጋላጭ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ለተከታታይ ዓመታት በጎርፍ እና በበረዶ እንደሚጠቃም አንስተዋል፡፡ የዘንድሮው ግን ከሁልጊዜው ለየት ይላል ነው ያሉት፡፡

ችግሩን የከፋ ያደረገው ደግሞ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር ነው ብለዋል፡፡ የታጠቁ ኀይሎች አርሶ አደሮች ግብዓት እንዳይወስዱ፣ የእርሻ ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይከውኑ አድርገዋቸው እንደከረሙም አንስተዋል፡፡ የታጠቁ ኀይሎች ወረዳውን ለከፋ ጉዳት እንደዳረጉት የተናገሩት አሥተዳዳሪው የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ሕዝቡ ተጎድቷል ነው ያሉት፡፡

ከሰሞኑ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከረጂ ድርጅቶች እና ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገ ውይይት ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲገባ መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡ መድኃኒት እና የሕጻናት አልሚ ምግብ መግባቱንም ገልጸዋል፡፡ ረጂ ድርጅቶች እና መንግሥት እያደረጉት ያለው ድጋፍ እየገባ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የሰብዓዊ ድጋፍ የዘገየው በታጠቁ ኀይሎች ጫና መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የታጠቁ ኀይሎች የሚያደርሱትን ጫና ማኅበረሰቡ ማስቆም እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ለእናቶች እና ለሕጻናት የምግብ ድጋፍ እና የጤና ክትትል እየተደረገላቸው መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ አልሚ ምግቡ እና መድኃኒት ከገባ ጊዜ ጀምሮ ያገገሙ ወገኖች መኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በቡግና ወረዳ ለተጎዱ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረሰ መኾኑን ከሰሞኑ መግለጹ ይታወሳል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደኅንነት ካሜራ
Next articleበቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት የተገነባው የደሴ ዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ።