
አዲስ አበባ: 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን 20 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የደኅንነት ካሜራዎችን ድጋፍ አድርጓል። ድጋፉን የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይታገሱ ደሳለኝ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ አስረክበዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ የተደረገው ድጋፍ የተቋሙን ደኅንነት ለማስጠበቅ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት የሚያደርገው ነው ብለዋል። ዋና ሥራ አሥፈጻሚው አሚኮ ታዓማኒ መረጃን ጥራት ያላቸው ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ለሕዝቡ ተደራሽ ለማድረግ ሁለቱ ተቋማት በቀጣይም በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ይታገሱ ደሳለኝ ተቋሙ የስማርት ሲቲ ትግበራን የሚያግዙ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለአማራ ክልል ከተሞች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። በዛሬው እለትም ለክልሉ ሚዲያ አሚኮ 20 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የደኅንነት ካሜራዎችን በድጋፍ ማበርከታቸውን ነው የተናገሩት።
ተቋማቱ በቀጣይም በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደረጉ ሲኾን የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት እየሠራቸው ያሉ ተግባራትም ተጎብኝተዋል።
ዘጋቢ: ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!