
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የበለጠ በመቀናጀት የሚሠሩበትን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። ስምምነቱን የፈረሙት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ እና የአማራ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ናቸው። ከሁለቱም ተቋማት በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎችም በስምምነቱ ላይ ተገኝተዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ እንዳሉት ሁለቱ ተቋማት ሁሌም ቢኾን በጋራ የሚሠሩ የሕዝብ አገልጋዮች ናቸው፤ ዛሬ የተደረገው ሥምምነትም አገልግሎትን የበለጠ ለማስፋት ያለመ የቤተሰብ ስምምነት እንጅ በማይተዋወቁ እንግዳ ተቋማት መካከል የተደረገ አይደለም ነው ያሉት። ሰነዱ በመቀራረብ እና በጋራ በማቀድ ሕዝብን መሠረት ያደረገ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ያግዛል ብለዋል።
ሁለቱም ተቋማት የሚያገለግሉት ሕዝብን ነው፤ ሕዝብን ስናገለግል ደግሞ በዕውቀት መኾን አለበት ነው ያሉት። በተለይም የጤና ጉዳይ የሰውን ሕይዎት በቀጥታ የሚነካ በመኾኑ አሚኮ ከኢንስቲትዩቱ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመኾን የቅድመ መከላከል መልዕክቶችን ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል። አሚኮ ብዝኀ ቋንቋ የሥርጭት አቅሙን በመጠቀም እና የጤና ዘርፍ ባለሙያዎችን በመጋበዝ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መረጃ ለሕዝብ እንደሚያደርስም አቶ ሙሉቀን ገልጸዋል።
ሕዝባችን ቀድሞ መከላከል በሚችላቸው በሽታዎች መጠቃት የለበትም፤ የሕክምና ወጭ የሕዝባችን ተጨማሪ ጫና መኾን የለበትም፤ ቅድመ የጤና ጥንቃቄዎችን ለማስገንዘብ እና የሕዝብን ጤና ለመጠበቅ አሚኮ የበለጠ ይተጋል ብለዋል ዋና ሥራ አሥፈጻሚው። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ዕውቀቱን በመሙላት አሚኮን እያገዘ ውጤታማ ሥራ እናከናውናለን ነው ያሉት።
አሚኮ በሁሉም የሥርጭት ቋንቋዎች መረጃ ሰጭ የጤና መልዕክቶችን እየቀረጸ እንደሚያስተላልፍም ተናግረዋል። የኢንስቲትዩቱ መሪዎች እና ባለሙያዎችም ከበፊቱም ሲያደርጉት የነበረውን ሙያዊ አስተዋጽኦ የበለጠ አጠናክረው በመቀጠል ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ሙሉቀን ሰጥዬ እንዳሉት በተናጠል ቆመን ጠንካራ ተቋማትን መገንባት አንችልም፤ ስለዚህ በጋራ በመቆም ለሕዝብ የሚሠሩ ሁነኛ ተቋማትን መገንባት ያስፈልጋል።
“ሕዝባችን ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጉታል፣ ይገባዋልም፤ ያንን ለማሳካት በጋራ እንሠራለን” ነው ያሉት። የዛሬውን የአሚኮ እና የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጋራ መግባቢያ ሰነድ እንዲሁ ተፈርሞ የሚረሳ ሳይኾን በተግባር የሚተረጎም እና ተጨባጭ ውጤት የሚያስገኝ አገልግሎት የሚሰጥበት እንደሚኾንም አቶ ሙሉቀን አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ ኢንስቲትዩቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመስርቶ እያደገ የሚገኝ የክልሉ ሕዝብ ተቋም ስለመኾኑ አብራርተዋል። ለዚህ ዕድገቱ ደግሞ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋነኛ አጋር ተቋም ኾኖ ሲያገለግል ቆይቷል፤ እያገለገለም ነው ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ሁለቱም ተቋማት ለአማራ ክልል ቁልፍ ጠቀሜታን የሚሰጡ የሕዝብ ተቋማት ናቸው፤ እነዚህ ቁልፍ ተቋማት የበለጠ ተቀናጅተው መሥራታቸው ለኅብረተሰቡ የጤና ስጋቶች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ጤናማ እና አምራች ማኅበረሰብ ለመፍጠር ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም አመላክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ የሚያናከናውናቸው የጤና ሥራዎች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ይኾኑ ዘንድ የሕዝብ ተሳትፎ እና ተግባቦት ወሳኝ ናቸው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ። ለዚህ ደግሞ አሚኮ የላቀ የሙያ ባለቤት ነው፤ በጋራ እና በመደጋገፍ እንሠራለን ብለዋል። አሚኮ እና ኢንስቲትዩቱ ያደረጉት ስምምነት ከሁለቱ ተቋማት አልፎ ለአማራ ክልል ሕዝብ ትልቅ ጥቅም የሚያስገኝ ስለመኾኑም አንስተዋል።
አሚኮ በፊትም የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ዋና አጋር ነው፤ አሁን የተደረገው ስምምነት በተደራጀ መልኩ ተግባራዊ ሥራዎችን ለማከናወን ያግዛል ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!