
ደሴ: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም(አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት የዞኖችን የአራት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል። ባለፉት አራት ወራት ውስጥ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ 91 በመቶ ማከናወን መቻሉን የደሴ ከተማ አሥተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቡድን መሪ ጌታቸው መሐመድ ገልጸዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ቡድን መሪ አደም ሰይድ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር መሻሻል መታየቱን ተናግረዋል። በቀጥይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ይሠራል ብለዋል። በጤና ተቋማት የወለዱ እናቶች ላይ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ማከናወኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው በለጠ ናቸው። አጋጣሚውን በመጠቀም የመዝገባ ተግባራት መሠራቱንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ገስጥ ጥላሁን በጤና ተቋማት የወሳኝ ኩነት አገልግሎትን ቀልጣፋ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተተገበሩ መኾኑን ተናግረዋል። የአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ኀላፊ መዓዛ በዛብህ በቀጣይ የወሳኝ ኩነት ምዝገባዎችን በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የዞን እና ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊዎች፣ የወሳኝ ኩነት ባለሙያዎች፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ኀላፊዎችን ጨምሮ ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ:- ሳልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!