
በበረሃማ የክልሉ አካባቢዎች ያለውን የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሻሻል እየሠራ ነው። ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እየተተገበሩ ያሉ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ያሉበትን አፈጻጸም ለማሻሻል ያለመ የመስክ ጉብኝት ተደርጓል።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር)፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ እና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ መሪዎች በአካባቢው እየተተገበሩ ያሉ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙት የጨፋ ሮቢት ከተማ እና የከሚሴ ከተማ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች በቀጣይ ጥቂት ቀናት የፍተሻ ሥራቸው ተጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገቡ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) ቢሮው በተያዘው በጀት ዓመት በገጠር እና በከተማ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የክልሉን ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ዶክተር ማማሩ አያሌው የጨፋ ሮቢት እና የከሚሴ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ያሉበት አፈጻጸም አበረታች መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ ቢሮ ኀላፊው አስረድተዋል። ቢሮው ከውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በርሃማ አካባቢዎች ያለውን የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሻሻል እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተገበረ መኾኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡ የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ እንደገለጹት ክልሉ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያሉ የመጠጥ ውኃ ተቋማት ያሉበትን ሁኔታ ገምግሞ ማስተካከያ በመስጠት የአካባቢውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ክልሉ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል። በቀጣይም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያለውን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የክልሉ ድጋፍ እንዳይለያቸው ጠይቀዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ ኀላፊ ሃሊማ ኡመር እንደገለጹት ቢሮው በተያዘው በጀት ዓመት የከሚሴ ከተማ እና የጨረቲ መጠጥ ውኃ ችግርን ለመፍታት እየሠራ ነው፡፡ በ35 ሚሊዮን ብር የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ነው የገለጹ፡፡ ቢሮው የብሔረሰብ አሥተዳደሩን መጠነ ሰፊ የመጠጥ ውኃ ችግር ለመፍታት በጀመረው አግባብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡ ቢሮው ላደረገው ድጋፍም በመምሪያው ስም ምሥጋና አቅርበዋል።
የጨፋ ሮቢት ከተማ አሥተዳደር ቢሮው የከተማውን ሕዝብ የረጅም ጊዜ የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ለመቅረፍ ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ቢሮው በጀመረው መንገድ ክትትል እንዲያደርግም ጠይቀዋል። የጨፋሮቢት ከተማ የመጠጥ ውኃ ተጠቃሚዎች ለበርካታ ዓመታት በንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ውስጥ የቆዩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ የተጀመረውን የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሠራ በመኾኑ የተሰማቸውን ደስታ መግለጻቸውን ከክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!