የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሕዝቡን ሕይዎት ለማሻሻል እንዲሠሩ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አሳሰቡ።

13

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ትምህርት ሚኒስቴር ከ47 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በ2017 በጀት ዓመት የሚተገበር ቁልፍ የአፈጻጸም ውል ተፈራርሟል። የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሠሯቸው ምርምሮች እና የሚያፈሯቸው ዜጎች ሀገር የሚለውጡ እና ከዓለም ጋር ተወዳድረው ማሸነፍ የሚችሉ ሊኾኑ ይገባል።

ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን ወደ ራስገዝነት እያሳደጉ ቀጣይነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸውም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የተፈረመው ውል ኀላፊነት እና ተጠያቂነትን በማስፈን የትምህርት፣ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን ጥራት ለማስጠበቅ እንደሚያስችልም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የትምህርት እና የምርምር ጥራትን በማስጠበቅ ብቃት እና ጥራት ያለው ዜጋ ማፍራት ግዴታ መኾኑን አውቀው በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በቁልፍ የአፈጻጸም መለኪያ ስምምነቱ መሠረት ውጤት የሚያስመዘግቡ ተቋማት በበጀት ጭምር የበለጠ የሚደገፉበት፣ ወደ ኋላ የሚቀሩ እና ዝቅተኛ አፈጻጸም የሚያስመዘግቡት ደግሞ ተጠያቂ የሚኾኑበት እንደኾነ ጠቁመዋል።

ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትርን በመወከል የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ አት ኮራ ጡሹኔ፣ ዩኒቨርሲቲዎቹን በመወከል ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎቹ ቦርድ ሠብሣቢዎች እና ፕሬዚዳንቶች ፈርመዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article”ሙስና እየከፋ ሄዶ ሀገር ማፍረስ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በትኩረት ሊሠራበት ይገባል” ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)
Next articleየአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ