
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ ፖሊስ ኮሚሽን እና ፍትሕ ቢሮ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር ሙስናን ለመታገል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። በውይይቱ ተቋማቱ ከሙስና አኳያ የሠሯቸውን ሥራዎች አቅርበዋል። በክልሉ ሙስና ያለበት ደረጃ እና ለመታገል እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችም ተነስተዋል። በቀጣይም ተቀራርቦ እና ተቀናጅቶ በመሥራት ሙስናን መከላከል ስለሚቻልበት ስልት ሃሳብ ቀርቧል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን ሙስናን ለመቀነስ ማኅበረሰቡም ኾነ የየደረጃው መሪ ስለ ሙስና ያለው አመለካከት ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል። ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች ጭምር በሙስና ሲዘፈቁ እንደሚታዩም ጠቅሰዋል። የወቅቱን የጸጥታ ችግር እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ከፍተኛ የሃብት ምዝበራ እየተፈጸመ ነው ያሉት ኮሚሽነር ደስዬ በተቋማቱ መሪዎች በኩልም የስብዕና መጓደል አለ ብለዋል። ሕዝቡ ያለ እጅ መንሻ አገልግሎት እያገኘ አለመኾኑንም ጠቅሰዋል።
የሃብት አመላለስ በሰላማዊ ጊዜም ችግር የነበረበት ነው፤ አሁን ደግሞ የበለጠ ልንቸገር እንችላለን፤ ስለኾነም በትኩረት መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል። ሥራውም ለሕግ አስከባሪ ተቋማት ብቻ የሚተው አለመኾኑንም ገልጸዋል። የትምህርት እና ሥልጠና ዘዴዎች እና የወንጀል መከላከል ትምህርት ምን መኾን እንዳለበት በግልጽ መቃኘት አለበት ነው ያሉት። ትግሉን የጋራ ለማድረግ አሠራር ሊበጅለት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ሙስና እየተስፋፋ እንደኾነ ተናግረዋል። ችግሩን ለመታገልም እየተወያዩ የመሥራት ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደኾነ ገልጸዋል። የሚቋረጡ የጸረ ሙስና የክስ መዝገቦች መብዛት ከሙስና ውሥብሥብነት ባህሪ የሚመጣ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ ሙስናን በሰው ምስክር ብቻ ለመታገል አስቸጋሪ መኾኑን የሚቋረጡ የክስ መዝገቦች እንደሚያሳዩ ነው ያብራሩት።
በተቋማት መካከል የሚፈጠረው የመረጃ መጣረስ ሌላኛው ሊፈታ የሚገባው ችግር እንደኾነ አመላክተዋል። መረጃን የምንቀበልበትን ተቋም አመራረጥም ላይ በቀጣይ መታየት አለበት ብለዋል። የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሐብታሙ ሞገስ የሙስና መከላከል ስትራተጂ ተዘጋጅቶ እና በመከላከሉ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል። ኮሚሽኑ የባለሙያዎች እጥረት እንዳለበት ያነሱት ኮሚሽነር ሐብታሙ በተመረጡ የሙስና ወንጀሎች ላይ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ተቀናጅቶ መሥራትም የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የትውልድ ግንባታ ላይም እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል። “ከራሳችን ጀምረን ሃብት ማስመዝገብ አለብን” ያሉት ኮሚሽነር ሐብታሙ ፖሊስም ሃብታቸውን የማያስመዘግቡ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ተባባሪ እንዲኾን ጠይቀዋል። የራስን ተቋም ንጹህ አድርጎ አርዓያ በመኾን በኩልም ኀላፊነት አለብን ብለዋል።
ውጤታማ መረጃዎችን በማግኘት በኩል ያለውን ውስንነት መቅረፍ ይገባልም ነው ያሉት ኮሚሽነር ሐብታሙ። ተቀናጅተን በየጊዜው እየገመገምን በመሥራት ውጤታማ እንኾናለንም ብለዋል። በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ሙስናን ለመከላከል በባለ ድርሻ አካላት መረጃ የመለዋወጥ ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል።
የጸረ ሙስና ትግሉ በተለያዩ ተቋማት ተበትኗል። ጸረ ሙስና ኮሚሽንም ለጸረ ሙስና ትግሉ እንደቀድሞው ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል። ሙስና እየከፋ በመሄዱ ሀገር ከማፍረስ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባም አሳስበዋል። የጸረ ሙስና ትግል ሥራዎችን ትኩረት ሰጥቶ በመተግበር እና በመቀናጀት መተባበር እንደሚገባም ነው ዶክተር ደሴ የተናገሩት። በጥቆማ፣ በምርመራ ጥራት እና በመዝገብ አያያዝ ላይ የትብብር ሥራ እንደሚፈልግ አመላክተዋል። በዘርፉ ላይ ጥናት የማድረግን አስፈላጊነትም አመላክተዋል።
የጥቆማ ሰጭዎችን ደኅንነት መጠበቅም ለጸረ ሙስና ትግሉ አጋዥ እንደኾነም አንስተዋል። ምክር ቤቱም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት። በመድረኩ ተቋማቱ ሙስናን በጋራ ለመታገል የሚያስችል የትብብር ሥምምነትም ተፈራርመዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!