“ብልጽግና ፓርቲ ለሕዝብ ቃል በገባው መሰረት በዘላቂ ሰላም ግንባታና አካታች ልማት ስኬቶችን አስመዝግቧል” ተመሥገን ጥሩነህ

34

ባሕር ዳር: ታኅሳስ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ ለሕዝብ ቃል በገባው መሰረት በዘላቂ ሰላም ግንባታና አካታች ልማት አበረታች ስኬቶችን ማስመዝገቡን የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ገለጹ። የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ በመደበኛ ስብሰባው ከመከረባቸው አጀንዳዎች መካከል ሰላምና ልማት ዋነኞቹ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ኢትዮጵያን ከግጭት አዙሪት ለማላቀቅ ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥትና አወንታዊ ሰላም ግንባታ ላይ ብዙ ርቀት መጓዙን አንስተዋል። ለውጡ ያልተዋጠላቸው አካላት የፈጠሯቸውን ግጭቶች በድርድርና በውይይት ማርገቡንም ገልጸዋል። ለአወንታዊ ሰላም ግንባታ መሳካትም ችግሮችን በሀገራዊ ምክክር ለመፍታት፣ የሽግግር ፍትሕና የተሐድሶ ተግባራትን ለማከናወን ተግባራዊ ቁርጠኝነቱን በማሳየት ላይ ነው ብለዋል።

መንግሥት ታጥቀው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ባደረገው ጥሪ መሰረት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በርካታ የታጠቁ ቡድኖች ወደ ሰላም በመምጣት የሀገር ጸጥታና ልማትን ለማረጋገጥ ዋነኛ ተዋናይ በመሆን ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል። ብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት ባለፉት ዓመታት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት በማጠናከር ከአንድም ሀገር ጋር ግጭት አለመግባቱንም በስኬት አንስተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የሀገርን ሰላምና ደኅንነት በዘላቂነት የሚያስጠብቁ ጠንካራ የጸጥታ ተቋማት መገንባታቸውን ገልጸዋል። ፓርቲው በአንደኛ ጉባኤው ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ልማቶችን እንደሚተገብር ቃል መግባቱን አውስተው በዚሁ መሰረት አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ ከውጭ የሚገባ ስንዴን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀረት የገባውን ቃል መፈጸሙን ጠቅሰው አሁን ላይ ወደ ውጭ መላክ ተጀምሯል ብለዋል። በቱሪዝም ዘርፉም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ገፅታ የቀየሩ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች በጥራትና በፍጥነት መተግበራቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ቁመው የነበሩ ፋብሪካዎች ሥራ መጀመራቸው፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት እና የማዕድን ዘርፉ ላይ መሰረታዊ ለውጦች መምጣታቸውንም ጠቅሰዋል። እንደ ምክትል ጠቅላይ ሚኒሥትሩ ገለጻ ፓርቲው የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በገባው ቃል መሰረት የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ዲጅታል በማስገባት ሲቪል ሰርቪሱን ሪፎርም ማድረግ ጀምሯል።

ፓርቲው እንደ ሀገር ያልተሻገርናቸውን ችግሮች በመፍታት አካታች የኢኮኖሚ እድገት፣ ዘላቂ ልማትና ሰላም ላይ ያስመዘገባቸውን ውጤቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ኢትዮጵያን እምቅ ጸጋዋን በመጠቀም ወደ ከፍታዋ ለመውሰድ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት እና በተባበረ ክንድ ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ የብልጽግና ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዳሽን ቢራ ፋብሪካ በቡግና ወረዳ ለተቸገሩ ወገኖች 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ፡፡
Next article“ከተሜነት መጭውን ዘመን የዋጀ እንድኾን ተደርጎ እየተሠራ ነው”አሕመድን ሙሐመድ(ዶ.ር)