የሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለሀገራዊ ሰላም በትብብር እንደሚሠሩ ገለጹ፡፡

35

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ (ዶ.ር) ከምክር ቤቱ መሪዎች እና የሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ትውውቅ እና ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ ላይ የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ (ዶ.ር) ለችግሮች መፍቻ የሚኾን ባሕል እና ልምድ ያላት ኢትዮጵያ ዜጎች በሰላም እጦት ምክንያት ለችግር መዳረግ የለባቸውም ብለዋል።

ዜጎች በሰላም እጦት ምክንያት ለችግር እንዳይዳረጉ የሃይማኖት ተቋማት ሚና የላቀ በመኾኑ ለሰላም ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል። በአፋር እና በሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የነበረውን አለመግባባት እና ግጭት ለመፍታት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለሠራው ገንቢ ሥራ ምሥጋና አቅርበዋል።

በተመሳሳይ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የኢትዮጵያን ስም በዓለም መድረክ ከፍ ለማድረግ እየሠሩ ያለውን ሥራም ሚኒስትሩ አድንቀዋል። ምክር ቤቱ ሁሉን አቀፍ የሰላም እና የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የሙስሊሙን አንድነት እና ሀገራዊ ሰላምን ለማጠናከር ጠቅላይ ምክር ቤቱ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ ከጥር 23 እስከ 25 /2017 ዓ.ም ይካሄዳል “አቶ አደም ፋራህ
Next articleዳሽን ቢራ ፋብሪካ በቡግና ወረዳ ለተቸገሩ ወገኖች 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ፡፡