
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም(አሚኮ) ሁለተኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ከጥር 23 እስከ 25 /2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና ዋና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደም ፋራህ ተናግረዋል። በአንደኛው የብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎችን በመፈጸም በኩል አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አደም ፋራህ ተናግረዋል።
ባለፈው የፓርቲው ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎችበኢኮኖሚ፣ በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊ፣ በዲፕሎማሲ፣ በአሰባሳቢ ትርክት ማዳበር፣ በሰላም እና ደህንነት በመሰል ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን በመፈጸም ፓርቲው ለሕዝብ የገባቸውን ቃሎች በማክበር እና በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በኢኮኖሚው የሀገር በቀል ማሻሻያዎችን በመተግበር እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲን በመከወን ተጨባጭ ለውጥ የታየባቸው ሥራዎችን መተግበር መቻሉን ጠቅሰዋል። የዓቅም ግንባታ ሥራዎች መሠራታቸው፣ አፈጻጸምን መሠረት በማድረግ የማበረታቻ እና የእርምት እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል። ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ጠንካራ የፌደራል ሥርዓት እንዲፈጠር መሠራቱን ጠቅሰዋል።
የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አንጻርም አበረታች ተግባራት መሠራታቸውን እና በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀርበው የሚነጋገሩበት ምህዳር መፈጠሩን አንስተዋል። በሂደቱ ያጋጠሙ ከሰላም ችግር ጋር የተያያዙ እና መሰል ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን በመቋቋም ሥኬቶች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል።
ለሁለተኛው ጉባኤ ዝግጅትም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ መኾኑን ከፓርቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!