
ሰቆጣ: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል መንግሥት ከፍተኛ ጥረት ከኮረም – ሰቆጣ – ትያ ያለው የጠጠር መንገድ ጥገና እና ግንባታ ሥራ እየተካሄደ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር መንገድ መምሪያ አስታውቋል። በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን ከኮረም – ሰቆጣ – ትያ (ላልይበላ መገንጠያ) 50 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው መንገድ ነው። መንገዱ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት በመስጠቱ ጉዳት እንደደረሰበትም ተመላክቷል።
የጠጠር መንገዱ ጥገና እና ግንባታ በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ይሁንታ በመሰጠቱ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ሥራውን ተረክቦ በተሻለ ፍጥነት ወደ ጥገና እና ግንባታ ተግባር መግባቱን መምሪያው ገልጿል። አሁን ላይ የጥገና ሥራው እና ግንባታው ከላሊበላ መገንጠያ (ትያ) – ኮረም 2 ኪ.ሜ መንገድ ጥገና አልቋል ነው የተባለው። የጥሬ እቃ ማምረት እና የድች ማውጣቱ ሥራ 10 ኪ.ሜ ላይ ደርሷል።
ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር መንገድ መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ የክልሉ መንግሥት ጫና፣ የአካባቢው አሥተዳደር ክትትል፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ትብብር የሚመሰገን ነው ተብሏል። ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ በጥራት እና መጠን እንዲጠናቀቅ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግም ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!