ሕገ ወጥ ንግድ በሕጋዊው ንግድ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል።

31

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 13 በአነስተኛ ንግድ ሥራ ተሰማርታ የምትገኘው ዓለም ደባልቄ ገበያዋ ቀዝቃዛ መኾኑን ትናገራለች፡፡ የግብርን ተገቢነት የምታምነው ዓለም በአዲስ የተጠናውን የቁርጥ ግብር ለመክፈል ሕገወጦች ችግር እንደኾኑባቸው ነው የምትናገረው።

ንግድ ፈቃድ ሳያወጡ እየተዟዟሩ የሚሠሩት ላይ ቁጥጥር ስለማይደረግ መሥራት አልቻልኩም፤ ካልሠራሁ ደግሞ የሚወሰነውን ግብር ለመክፈል እቸገራለሁ ነው ያለችው። ”ሕግ ከምናከብረው ይልቅ ሕገ ወጦቹ እየከበሩ እንዴት ግብር እንክፈል?” ስትልም ትጠይቃለች። ደጉ ሞላ ደግሞ ልብሶችን እያዞረ ይሸጣል። በጎዳና ላይ የመሥራትን ሕገ ወጥነት ያውቃል። ደንብ አስከባሪዎችን ባየ ቁጥር ሩጫው እንደሰለቸው ነው የተናገረው። መንግሥት የመሥሪያ ቦታ ቢሰጠው ዛሬ ነገ ሳይል ሕጋዊ ኾኖ መሥራት እንደሚፈልግም ነው የገለጸው።

”ደንብ አስከባሪዎች እኛን ማባረር እና መውረስ ብቻ ነው ሥራቸው” ያለው ደጉ ሕጋዊ ኾነን እንድንሠራ ማንም አነጋግሮን አያውቅም ነው ያለው። ለመኖር መሥራት አለብን፤ በመንገድ አትሠሩም ከተባልን የምንሠራበት ቦታ ሊሰጠን ይገባልም ብሏል። በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የደንብ ማስከበር መምሪያ የደንብ መተላለፍ ቁጥጥር ቡድን መሪ መብራቴ ቢምረው ከአራት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት በባሕር ዳር በሦስት ቀበሌዎች ብቻ 800 ሕገ ወጥ ነጋዴዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

በከተማ አሥተዳደሩም የመሥሪያ ቦታ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል። በቅርቡ የተጠና መረጃ ባይኖርም የሕገ ወጥ ነጋዴው ቁጥር በርካታ መኾኑን ነው የተናገሩት። አሁን ላይ በተሠራ ሥራ የንግድ እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው ቀበሌ 04 እና 05 እንዲሁም ከጊዮርጊስ እስከ ፓፒረስ፣ ከፓፒረስ እስከ አዝዋ አካባቢዎች ሕገ ወጥ ንግድ መቆሙን ነው የገለጹት።

ሕገ ወጦች የሰው እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው አካባቢዎች እየተዘዋወሩ በመሸጥ የሕጋዊ ነጋዴዎችን ጥቅም እንዳይቀሙ ለማድረግ ችለናል ብለዋል። በቀበሌ 11፣ 14 እና በሌሎች የከተማው ክፍሎች ሕግ የማስከበሩ ሥራ በቂ አለመኾኑን የገለጹት ቡድን መሪው በባሕር ዳር ሕገ ወጥ ንግድን ለማስቀረት ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል። ነገር ግን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንቅፋት ኾኗል ብለዋል።

ደንብ ማስከበር እየተሠራ ያለው እያዞሩ ወይም በመንገድ ዳር ዘርግተው የሚሸጡ ሕገ ወጦችን እንደኾነ አቶ መብራቴ ጠቅሰዋል። የንግድ ፈቃድ ሳያወጡ ሱቅ ከፍተው የሚሠሩትን ደግሞ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያው ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓቱ እንደሚያስገባቸው ገልጸዋል። ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል አምሽቶ፣ ቅዳሜ ፣ እሑድ እና በበዓላት ቀንም መሥራትን የሚጠይቅ ነው ያሉት ቡድን መሪው በደንብ ማስከበር ያለው የሰው ኀይል በቂ አለመኾኑን ገልጸዋል።

አብዛኛው ነጋዴም ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ተባባሪነቱ አነስተኛ መኾኑን ነው የጠቀሱት። የራሱ ጥቅም ለሚከበርበት የሕገ ወጥ ንግድ የመከላከል ሥራ ሊተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል። በቀበሌ 04 በአክሲዮን የሚሠሩ ነጋዴዎች ለደንብ አሥከባሪ ገንዘብ አዋጥተው ከተማ አሥተዳደሩ ቀጥሮ ደንብ እንዲከበርላቸው የሚሠሩ መኖራቸውንም በአብነት አንስተዋል።

ግንዛቤ እየተፈጠረ በሂደት መሻሻል እየታየ መኾኑንም አስረድተዋል። ዘላቂ መፍትሔው ወጣቶች በሕጋዊ መንገድ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው ብለዋል። በአብዛኛው ሕገ ወጥ ንግድ የሚበዛው የሕዝብ ፍሰት ባለበት አካባቢ ነው ያሉት ቡድን መሪው ለደንብ አስከባሪዎችም መመሪያ በመስጠት የክትትል ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ አደራ ጋሼ በሕገ ወጥ ንግድ የተሰማሩትን ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት ለማስገባት በሕገ ወጥ ንግድ መከላከል እና ጸረ ኮንትሮባንድ ግብረ ኀይል አማካኝነት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህ ዓመትም 26 ሺህ 987 ነጋዴዎች ፈቃዳቸውን እንደሚያድሱ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ሱቅ እና አድራሻ ኖሯቸው የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚነግዱትን ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓቱ እንዲገቡ በመከታተል እና ግንዛቤ በመፍጠር ፈቃድ እንዲያወጡ እየተሠራ ነው ብለዋል። ”ንግድ ፈቃድ ሳያወጡ መነገድ ወንጀል ነው” ያሉት አቶ አደራ ነገር ግን የኅብረተሰቡ ግንዛቤ አነስተኛ በመኾኑ ሱቁን ከማሸግ ይልቅ ማስተማርን እና ፈቃድ እንዲያወጣ ማድረግን ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል። ከደንብ ማስከበር ጋር በመቀናጀት ሥርዓት ለማስያዝ እየተሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የሕገ ወጥ ንግድ መከላከል እና ጸረ ኮንትሮባንድ ግብረ ኀይል እየተከታተለ እንደሚገኝም ተናግረዋል። የንግድ ምዝገባ፣ ፈቃድ እና የክትትል ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መምሪያ ኀላፊው አረጋግጠዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
Next articleከኮረም – ሰቆጣ – ትያ የመንገድ ጥገና እየተካሄ ነው።