
እንጅባራ: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች የደለቡ እንስሳት እና የእንስሳት ተዋፅኦዎች ዐውደ ርዕይ ተካሂዷል። በዐውደ ርዕዩ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች፣ ከወረዳዎች እና ከከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ገበየሁ በሪሁን በወረዳው በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ ያለውን ፀጋ በአግባቡ ለመጠቀም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በወረዳው ባለፉት ስድስት ወራት አርሶ አደሮች በሬዎችን፣ በጎችን፣ ንብ እና ዶሮዎችን እንዲያረቡ እና እንዲያደልቡ ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በተሠራው ሥራ 2 ሺህ 761 አርሶ አደሮች አሟልተው መገኘታቸውን ነው የገለጹት። ለሥራው ስኬታማነት የተጠናከረ የአመራር እና የባለሙያ ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱንም ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ፀር የኾኑ ድህነት እና ጽንፈኝነትን በጋራ መታገል ይገባል ብለዋል።
ብሔረሰብ አሥተዳደሩ የበርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤት ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት። ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ድህነትን ማሸነፍ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል። ከሰላም ሥራ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎችን ማሳለጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዐውደ ርዕዩ ለሌሎች ልምድ ለማካፈል እና አምራቾችን ከሸማቾች ጋር በማገናኘት የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዝ የአካባቢው አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!