
አዲስ አበባ: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ውጤታማነት በሚያገለግሉ ግብዓቶች ፍላጎት፣ አቅርቦት መካከል ያሉትን ክፍተቶች ለመለየት እና የመፍትሔ ሃሳብ ለማስቀመጥ ያለመ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ ፈንታ ደጀን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ወሳኝ ዘርፍ ነው ብለዋል። መንግሥት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ እና ጠንካራ አመራር በመስጠት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዘርፉ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ፣ ገበታ ለሸገር፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የደኅንነት ተቋማት ሕንጻዎች፣ የተቀናጀ የኮሪደር ልማት፣ የባሕር ዳር ዓባይ ድልድይ፣ የኢንዱስትሪ መንደር፣ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና መሰል ፕሮጀክቶች በዘርፉ የተመዘገበው ውጤት ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች የኢንዱስትሪውን እምቅ አቅም የሚያሳዩ ቢኾንም፣ ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ፣ በግንባታ ጥራት የሚታየው ጉድለት፣ የቅንጅት ማነስ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዝቅተኛ መኾን፣ የተቋራጮች እና የአማካሪዎች አቅም ማነስ፣ የግንባታ ግብዓት እጥረት እና የዋጋ ንረት፣ ደካማ የግንባታ ፕሮጀክት አሥተዳደር የዘርፉን ውጤታማነት ጥያቄ ውስጥ ከተውታል ብለዋል።
ዘርፉ ያለበትን ውስብስብ ችግር ለመፍታት እና በውጤታማነት ለማስቀጠል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እና በትብብር ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት። የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ዴኤታ የትምጌታ አስራት የመንገድ፣ የቤት፣ የድልድይ እና ሌሎች ግዙፍ የሕንጻ ፕሮጀክቶችን ስንገነባ ሀገር ነው የምንገነባው ብለዋል።
የግንባታ ፕሮጀክቶች በጥራት፣ በብቃት እና በታማኝነት በታለመላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ ረገድ ውስንነቶች እንዳሉም አንስተዋል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዘርፈ ብዙ ውሥብሥብ ችግር ውስጥ እንዳለ የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው በተቀመጡ የፖሊሲ ማዕቀፎች ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እና በትብብር መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል።
ለቀጣዩ ትውልድ የሚጠቅሙ ዘመን ተሻጋሪ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቁርጠኛ ኾኖ ወደ ሥራ መግባቱንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!