
ጎንደር: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር በቀልጣፋ ንግድ ሂደት እና የሚታዩ ክፍተቶችን መሙላት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከከተማዋ ነጋዴዎች ጋር እየመከረ ነው። በውይይቱ የመክፈቻ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ግርማይ ልጃለም ነጋዴው ማኅበረሰብ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ ኾኖ በመነገድ የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሊያሳድጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቴዎድሮስ ጸጋዬ የንግዱ ማኅበረሰብ በሕጋዊ አሠራር እየተደራጀ ጠንካራ አቅም መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል። የጥምቀት በዓል የንግዱን ማኅበረሰብ ጨምሮ ሁሉንም የከተማው ማኅበረሰብ የሚያነቃቃ በመኾኑ በአገልጋይነት መንፈስ መነገድ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መምሪያው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፈቃድ ማውጣት እና እድሳት፣ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች ማስወገድ፣ የገበያ ማዕከላትን ማስፋፋት እና ሌሎችን ሥራዎችን እየሠራ መኾኑ ተነስቷል። የንግድ ፈቃድ መቀያየር፣ ባዕድ ነገር መቀላቀል፣ ተገቢ ባልሆነ ሚዛን መሸጥ፣ ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድ፣ ደረሠኝ አለመቁረጥ ደግሞ በንግዱ ማኅበረሰብ በኩል የታዪ ችግሮች መኾናቸውን ጠቁመዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የኾኑ ነጋዴዎች በበኩላቸው በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን አንስተዋል። በተለይ የጸጥታ ችግሩ ሸቀጥ ለማስገባት ያለው እንግልት ከባድ መኾኑን ጠቅሰው የተቀዛቀዘ ግብይት መኖር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እና ከከተማው የሥራ ኀላፊዎች ጋር ተቀራርቦ በሚፈለገው መጠን አለመሥራት ለንግዱ እንቅስቃሴ ፈተና መኾናቸውን ተናግረዋል።
ለወደፊቱም መፈታት ያለባቸው ችግሮች ተለይተው መፍትሔ እንዲሰጥባቸው ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!