በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡

29

ደብረ ማርቆስ: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ማኅበረሰቡ የሰላም ባለቤት በመኾን አካባቢውን በንቃት ተደራጅቶ እንዲጠብቅ አሳስቧል። የተከሰተውን የሰላም እጦት እንደምክንያት በመጠቀም በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን አሳድረዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ይሄነው አበባው ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን በከተማዋ የሚፈፀሙ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የቁጥጥር እና የክትትል ተግባር እየተሠራ ነው ብለዋል። በተሠራው ሥራም በስርቆት እገታ እና ዝርፍያ የተሠማሩ ግለሠቦች ላይ ሕጋዊ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

የጸጥታ መዋቅሩን በማጠናከር ማኅበረሰቡ የዕለት ከዕለት ተግባሩን ያለምንም ስጋት እንዲያከናውን በከተማዋ የሰላም ማስከበር ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡ ለጸጥታ ኀይሉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለጹት ኀላፊው ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት በመኾን አካባቢውን ተደራጅቶ በንቃት እንዲጠብቅ ተደርጓልም ነው ያሉት። ይህን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

ማኅበረሰቡ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን የሚፈፀሙ ግለሰቦችን በመከታተል እና ጥቆማ በመስጠት ተባባሪ እንዲኾንም ጠይቀዋል። ከጸጥታ ኀይሉ ጎን በመሰለፍ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍትሕ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት የጸረ ሙስና ትግሉን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
Next articleየሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀትን 69 በመቶ ገደማ መቀነስ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።