ከፍትሕ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት የጸረ ሙስና ትግሉን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።

27

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሙስናን ለመከላከል እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ከፍትሕ ቢሮ እና ከፖሊስ ኮሚሽን ጋር ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጠናከር ውይይት አድርጓል። የመግባቢያ ሠነድም ተፈራርሟል። በውይይቱ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስየ ደጀን፣

የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከተሰጡት ተግባራት ውስጥ አንዱ ሙስናን መከላከል መኾኑን ጠቅሰዋል። በዚህ ተልዕኮም ትውልድን በመልካም ሥነ ምግባር ማነጽ እና ዜጎች ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና፣ ፍትሕ እና ፖሊስ ተቋማት ተቀናጅተው በመሥራት ተልዕኳቸውን ዳር ለማድረስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይቱ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል። ችግሮችን ገምግሞ በማረም ለመሥራትም እንደሚያስችል ተናግረዋል። ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በምዝገባ እና መረጃ አያያዝ ውስጥ የሚያገኛቸውን መረጃዎች የሚቀበል እና የፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ አጣርቶ ለሕግ በማቅረብ በኩል እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን በመወያየት መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ወደፊትም ከሌሎች የፍትሕ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት የጸረ ሙስና ትግሉ መጠናከር አለበት ብለዋል።
የሙስና ተግባራትን የሕግ ተጠያቂነት ከፍ ለማድረግ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴም የጸረ ሙስና ትግሉ ውጤታማ እንዲኾን እየተከታተለ እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሐብታሙ ሞገስ ኮሚሽኑ በሕግ በተሰጡት ሥልጣን እና ተግባራት መሠረት የሥነ ምግባር ግንባታ፣ የሙስና መከላከል እና የሃብት ምዝገባ እና ማጣራት ተግባራትን እንደሚያከናውን ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታትም እነዚህን ተግባራት ሲፈጽም መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ሙሰና በሀገር ምጣኔ ሃብት፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሥርዓት ላይ ችግር እያስከተለ መኾኑንም አስገንዝበዋል። ባለፉት ዓመታት በርካታ የሙስና ወንጀሎች ተፈጽመዋል ነው ያሉት። ወንጀሎቹን በመመርመር እና በማጣራት ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ የውይይቱ ተሳታፊዎች ትልቅ ሚና አላቸው ነው ያሉት።

በተያዘው በጀት ዓመትም የተቋማት ነጻነት እንደተጠበቀ ኾኖ ከፖሊስ እና ከፍትሕ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት በሚቻልበት ኹኔታ ላይ ለመወያየት መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። በውይይቱ ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሙስናን ለመታገል እና ሙሰኞችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሠራቸውን ሥራዎች እና ያጋጠሙትን ችግሮች ለውይይት አቅርቧል።

ፖሊስ ኮሚሽንም ሙስናንን ለመከላከል በትኩረት እየሠራ መኾኑ ተመላክቷል። የተሠሩ የምርመራ መዝገቦች እና ከምዝበራ የዳነ የሃብት መኖሩም ተገልጿል። በፍትሕ ቢሮ በኩል በቀረበ የመወያያ ሃሳብም በጸረ ሙስና ትግሉ የተሠሩ ሥራዎች፣ በቀጣይ በቅንጅት ሊሠሩ እና ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ተመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመር የልደት በዓልን ለሚያከብሩ ወገኖች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
Next articleበደብረ ማርቆስ ከተማ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡