
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የፍትሕ ትራንስፎርሜሽን ቋሚ ኮሚቴ የፍትሕ ተቋማትን የአምስት ወር አፈፃፀም ገምግሟል። በግምገማው ወቅትም የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው የቃል ክርክርን ወደ ጹሑፍ የሚቀይር የዲጅታል ቴክኖሎጅ በተቋማቸው ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
የዳኝነት ተደራሽነትን ማጠናከር፣ ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር፣ የዳኝነት አገልግሎት ጥራት እና ቅልጥፍናን ማሻሻል፣ የዳኝነት ነፃነት፣ ገለልተኝነት እና ግልፀኝነት ከተጠያቂነት ጋር ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እየተሠራ ነውም ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ የሙስና መከላከል ስትራቴጅ፣ የሥነ ምግባር እና የዲሲፕሊን ደንቦች፣ የቀጠሮ ፓሊሲ ማዘጋጀት፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ማጠናከር፣ የሀገር ሽማግሌዎችን ድርሻ ማሳደግ እና የፍርድ ቤቶችን አደረጃጀት የመከለስ ሥራ እየተሠራ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግንዛቤ እና ትግበራን፣ የሪፎርም ሥራዎችን እና የፈጠራ ሥራዎችን በዞን ከተሞች ተግባራዊ ማድረግ ስለመጀመራቸውም ነው ያብራሩት። የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም በፍትሕ ቢሮ በኩል ለ3 ሺህ 100 ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ግንዛቤ መፍጠር ስለመቻሉ አብራርተዋል።
51 ጉዳዮችን በማጣራትም በ20 የወረዳ እና የዞን ዐቃቢያን ሕግ በዲሲፕሊን ግድፈት ርምጃ ስለመወሰዱ ነው የተናገሩት። 22 የዞን ዐቃቢያን ሕግ በዲሲፕሊን ጉዳያቸው በሕግ እየታየ ስለመኾኑ የገለጹት ኀላፊው አመራር ማጥራት እና ማብቃት ለፍትሕ ሥርዓቱ ወሳኝ በመኾኑ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት እና ፍትሕ ላይ ለውጥ ለማምጣት በቅንጅት እየተሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። ጊዜ፣ ሃብት እና የሰው ኀይል መቆጠብ ስለመቻሉም ነው የተናገሩት። የታራሚዎችን ችግር ለማቃለል በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በሕክምና፣ በመኖሪያ እና ምግብ የተሻለ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ነው ያስገነዘቡት።
ሁሉም ማረሚያ ቤቶች የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ስለመደረጉም ጠቁመዋል። የፖሊስ መዋቅሩን ማደራጀት፣ ማዘመን፣ የሕክምና፣ የማዕረግ ጥቅማጥቅሞችን ማሻሻል ላይ እየተሠራ እንደኾነ እና ክልሉ የገጠመውን የመርማሪ እና የትራፊክ ፖሊስ ችግር ለመፍታት በልዩ ትኩረት መመራት አለበት ነው ያሉት ።
የፍትሕ ማሠልጠኛ ተቋሙ ካልተጠናከረ የክልሉ የፍትሕ ተቋማት እየገጠማቸው ካለው የሰው ኀይል ፍልሰት ጋር ተዳምሮ በሞያው የበቃ የሰው ኀይል እጥረት ሊገጥም ስለሚችል እንዲታሰብበት አሳስበዋል። የአማራ ክልል ምክር አቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በመድረኩ የተቋማቱ ቅንጅት እና በሁሉም ተቋማት እየተዘጋጁ ያሉ አዋጆች እና ሕጎች እንዲሁም የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን የተጀመሩ ጥረቶች የሚበረታቱ ናቸው ሲሉ አድንቀዋል።
ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶችን ማጠናከር፣ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴን ተደራሽ ማድረግ፣ ተቋማዊ አሠራሮችን ሕዝብ እንዲያውቃቸው ማድረግ፣ በሥራዎቻችን ሕዝብን ማሳተፍ ይገባል ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ። ሥልጣን በሕዝብ እና በአሠራር ካልተገራ ጥሩ እንደማይኾንም ነው ያስረዱት።
የፍትሕ ማሠልጠኛ ተቋሙ የሕዝብ እና የመንግሥት ጥቅም ለማረጋገጥ ብሎም የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሳደግ ወሳኝ ነው ብለዋል። የምርምር ማዕከል ሊኾን የሚገባው ተቋም በመኾኑ በጋራ ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!