“ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለአማራ ሕዝብ ያመጣውን ዕድል አናባክነውም” በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

22

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ የተወያየው የአማራ ክልልን ሰላም ለማረጋገጥ እና የክልሉ ሕዝብ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በብቃት እና በንቃት እንዲሳተፍ ለማድረግ ነው፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ በተወያየባቸው ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች በጋራ ለመሥራት መስማማቱም ተመላክቷል፡፡ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሣቢ ተስፋሁን ዓለምነህ ሀገራዊ ምክክር እንደ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ የሚመጣ ባለመኾኑ በተገቢው መንገድ መጠቀም አለብን ብለዋል፡፡

የዋሉ ያደሩ ጥያቄዎች የሚመለሱበት፣ የሚቃረኑ ፍላጎቶች፣ ጫፍ እና ጫፍ የሚሳሳቡ ሃሳቦች ወደ አንድ የሚመጡበት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነው ብለዋል፡፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሕዝብ ትክክለኛ ጥያቄ የሚመለስበት ትክክለኛ መድረክ መኾኑን ያነሱት ሠብሣቢው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን መደገፍ ለስኬቱ ያልተቆጠበ ድጋፍ ማድረግ እንዳለብን ተስማምተናል ነው ያሉት፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማ እንዲኾን ተሳትፏችን የበቃ እና የነቃ እንዲኾን ተስማምተናል ብለዋል፡፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ብዙ ችግሮችን የሚያስተካክል፣ ብዙ ፍላጎቶችን የሚያስታርቅ በመኾኑ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን መደገፍ አለብን ነው ያሉት፡፡ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሕዝብን ጥያቄ በጋራ ይዘው ለመቅረብ እና ስኬታማ ውጤት ለማግኘት በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በምክክር ኮሚሽኑ በሚኖራቸው ተሳትፎ በተናጠል እና በቡድን እንደሚሳተፉም ተናግረዋል፡፡ አለ የሚባለውን የሕዝብ ጥያቄ ለማቅረብ፣ ውይይት እና ድርድር የፖለቲካ መሳሪያቸው መኾኑን ለማሳየት ተስማምተናል ነው ያሉት፡፡ ሕዝብ ከሰላም፣ ከልማት እና ከዴሞክራሲ ተጠቃሚ መኾን ይፈልጋል ያሉት ሠብሣቢው የፖለቲካ ፓርቲዎች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሀገርን እንደ ሀገር ለማስቀጠል የጋራ አቋም መያዙን አስረድተዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግል የመጣ የለውጡ አካል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ለዘማናት ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች መኖራቸውን የተናገሩት ሠብሣቢው የአማራ ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የማቅረብ ዕድል አለ ብለዋል፡፡ “ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ያመጣውን ዕድል አናባከነውም፣ የተደራጀ ሃሳብ አለን፣ ሃሳባችን ዕውነተኛ የሕዝብ ጥያቄ ነው” ብለዋል ሠብሣቢው፡፡

የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ወደ ምክክር ኮሚሽኑ እንዲቀርብ እና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በትኩረት እንሠራለን ነው ያሉት፡፡ የምክክር ኮሚሽኑ ያመጣውን ዕድል እና በትግል የተገኘን መድረክ ማባከን አይገባም ብለዋል፡፡ ሕዝባችንን አስተባብረን የሀገራዊ ምክክር መድረኩን የትግል ሜዳ እናደርገዋለን፣ ተፈላጊውን ውጤትም እናመጣበታለን የሚል ዕምነት አለን ነው ያሉት፡፡

የሀገርን አንድነት እና ሉዓላዊነት በማይነካ መልኩ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመወያየት ዕውነትን በማስረዳት የጋራ የሚባል መፍትሔን ለማምጣት እንሠራለን ብለዋል፡፡ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ቀናዒ አመለካከት እንዳላቸው እና ለውጤታማነቱ እንደሚሠሩም አስታውቀዋል፡፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ የሚሳተፉበት አለመኾኑንም አንስተዋል፡፡

አሳታፊነቱ ትልቅ በኾነ መድረክ በብቃት እና በንቃት መሳተፍ ደግሞ ወርቃማ ዕድል ነው ብለዋል፡፡ ለሕዝብ ጥያቄ መፍትሔ የሚኾን እና ተስፋ የሚሰጥ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንደሚመለሱ እናምናለን፣ መድረኩንም በተገቢው መንገድ እንጠቀመዋለን ብለዋል፡፡ የጋራ በሚያደርጉን ጉዳዮች በጋራ እንሠራለንም ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሥራ አሥፈጻሚ አባል ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የአማራ ሕዝብ የዘመናት እና አሁናዊ ጥያቄዎች የሚፈቱት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ጥያቄዎቹ የሚፈቱት በንግግር፣ በውይይት እና በሰጥቶ መቀበል መኾኑን አመላክተዋል፡፡

ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን የተሠሩ ሥራዎችን ለማጠናከር እና በቀጣይ የሕዝቡ ተሳትፎ ሙሉ እንዲኾን የበኩላቸውን ለመወጣት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ገልጸዋል፡፡ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ጥያቄያቸውን ይዘው እንዲመጡ፣ እንዲወያዩ እና በክልሉ ያለው ችግር በሰላም እንዲቋጭ የጋራ ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል ነው ያሉት፡፡

የአማራ ሕዝብ በሀገራዊ ምክክሩ አይነተኛ ተሳትፎ እንዲኖረው እና ውጤታማ እንዲኾን በጋራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡ ጫካ የሚገኙ ኀይሎች ሰላምን መርጠው በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለማስመለስ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ሢሠሩ የቆዩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በባሕር ዳር እየተገነባ ያለውን የኮሪደር ልማት ጎብኝተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በሰላም ነው” በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
Next articleየሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሀገራዊ የሰላም ግንባታ ሥራዎች በጋራ እንደሚሠሩ ገለጹ።