“የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በሰላም ነው” በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

38

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ የተወያየው የአማራ ክልልን ሰላም ለማረጋገጥ እና የክልሉ ሕዝብ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በብቃት እና በንቃት እንዲሳተፍ ለማድረግ ነው፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ በተወያየባቸው ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች በጋራ ለመሥራት መስማማቱም ተመላክቷል፡፡ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሣቢ ተስፋሁን ዓለምነህ በወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ያለን ተሳትፎ ምን መምሰል አለበት? ሚናችንስ ምን መኾን አለበት? በሚለው ጉዳይ መክረናል ነው ያሉት፡፡

በክልሉ የሚታዩ የሰላም ችግሮች እና ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ የሰላም፣ የልማት እና የፖለቲካ ጥያቄዎቹ ሊፈቱ የሚችለው በሰላም እንደኾነ፣ ብቸኛ አማራጭ ሰላም እንደኾነ እና ከዚያ ውጭ የኾነ አካሄድ ተገቢ እንዳልኾነ ተግባብተናል ነው ያሉት፡፡ ግጭት ሕዝባችንን የሚያጎሳቁል፣ የሚያሳንስ፣ ከሕዝባችን ፍላጎት ጋር የሚቃረን መኾኑን መክረናል ብለዋል፡፡

የመንግሥት ተቀዳሚ ዓላማው የዜጎችን ሰላም ማስጠበቅ መኾኑ ታውቆ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ አለበት ነው ያሉት፡፡ ሕዝብም ለሰላም የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለክልሉ ሰላም መረጋጋጥ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አመላክተዋል፡፡

የመንግሥትን የሰላም እንቅስቃሴ እየደገፍን ጎን ለጎን ደግሞ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሎቻችን ለመቀጠል ተስማምተናል ነው ያሉት፡፡ ሰላምን ለሕዝብ ማምጣት እንዳባቸው ሰፊ ውይይት አድርገው መግባባታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሥራ አሥፈጻሚ አባል ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እና ቀውስ ለመፍታት ጥልቅ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በርካታ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል ነው ያሉት፡፡ የጸጥታ ችግሩ ሕዝብን ለከፍተኛ ጉዳት እንደዳረገው መምከራቸውንም ገልጸዋል፡፡ ችግሮች በንግግር፣ በውይይት እና በሰላም እንዲፈቱ በሚያስችሉ አቅጣጫዎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገናል ነው ያሉት፡፡

በክልሉ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም እንዲገኝ የጋራ ምክር ቤቱ የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸዋል፡፡ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የመፍትሔ ሃሳብ በማስቀመጥ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡ ሕዝብ የሰላም ባለቤት እንዲኾን እና ሰላሙን እንዲጠብቅ መሥራታቸውንም አመላክተዋል፡፡ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኀይሎችም የሰላም አማራጮችን እንዲጠቀሙ የጋራ ምክር ቤቱ መሥራቱን ገልጸዋል፡፡ በተሠራው ሥራ በርካታ ኀይሎች የሰላም አማራጭን ተጠቅመዋል ነው ያሉት፡፡

አሁንም ሰላማዊ አማራጮችን ተቀብለው በሥልጠና ማዕከል ውስጥ የገቡ መኖራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ አሁን ላለው ሰላም ዓይነተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ ሕዝብን የማንቃት እና የማደራጀት ሥራ መሥራቱንም ገልጸዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ በሰላም እንዲፈታ በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀሳቸውን ነው ያመላከቱት፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲነቃቃ እየሠራን ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)
Next article“ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለአማራ ሕዝብ ያመጣውን ዕድል አናባክነውም” በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት