“የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲነቃቃ እየሠራን ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)

45

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በባሕር ዳር ከተማ እያከናወናቸው ያሉ የግንባታ ሥራዎች ያሉበትን እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ፣ የገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማሕሙድ እና ሌሎችም መሪዎች በምልከታው ላይ ተገኝተዋል።

መሪዎቹ ከተመለከቷቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የእናቶች እና ሕጻናት ሕክምና ክፍል ግንባታ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ባለ ዘጠኝ ወለል ሕንፃ እና የቤዛዊት ሸኔል ሆም የሕንጻ ተገጣጣሚ አካል ማምረቻ ፋብሪካ ይገኙበታል።

ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እና በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የዛሬው የመስክ ምልከታ የኮርፖሬሽኑን የተግባር እንቅስቃሴ ለማየት እና ለመገምገም የሚያስችል ነው ብለዋል። ኮርፖሬሽኑ በግንባታ ቴክኖሎጂ እና በግብዓት አቅርቦት በኩል ያለውን ቁመና አይተናል፤ በተጨባጭ የሚሠራቸውን ፕሮጀክቶች ፍጥነትም በመስክ ምልከታ አረጋግጠናል ነው ያሉት።

ዶክተር አሕመዲን የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የእናቶች እና ሕጻናት ሕክምና ክፍል ግንባታ በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት መቆየቱን ጠቅሰው አሁን ላይ ችግሮች ተቀርፈው በጥሩ የግንባታ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል። ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት እንዲገባ በሌሊት ጭምር ሥራውን ለማከናወን አቅጣጫ መቀመጡንም አመላክተዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ለባሕር ዳር ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የሚያስገነባው ሕንጻም በፍጥነት እየተሠራ ስለመኾኑ አንስተዋል። ይህ ግንባታም ቀን ከሌሊት ተሠርቶ በቅርብ እንዲጠናቀቅ የሥራ አመራር ቦርዱ እና የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል ብለዋል። ሌላው ምልከታ የተደረገበት የቤዛዊት ሸኔል ሆም የሕንጻ ተገጣጣሚ አካል ማምረቻ ፋብሪካም በተለይም ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጅን ከመጠቀም አኳያ ተሞክሮ የሚቀሰምበት ስለመኾኑ ተናግረዋል።

ይህ የግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ፋብሪካ ተገጣጣሚ ሕንጻዎችን በአጭር ጊዜ ለመሥራት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን የሚያመርት ነው ብለዋል። ወጭን እና ጊዜን በቆጠበ መልኩ ቤት ለመገንባትም ጉልህ ሚና አለው ነው ያሉት። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲነቃቃ እየሠራን ነው ብለዋል። የግንባታው ዘርፍ ለሥራ ፈጠራ፣ ለኢኮኖሚ ግንባታ እና ለከተሜነት መሥፋፋት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉም ተናግረዋል። እንደ ክልል መንግሥት ዘርፉ ላይ ያሉ ቁልፍ ባለ ድርሻ አካላት እየተገናኙ ችግሮችን እየፈቱ ስለ መኾኑም ተናግረዋል። ይህም የክልሉ አጠቃላይ የግንባታ ዘርፍ በቶሎ እንዲጠናቀቅ እና ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ያስችላል ነው ያሉት።

ዘመን ኮንስትራክሽን በውል የያዛቸውን የክልሉ ፕሮጀክቶች በፍጥነት በማጠናቀቅ ለግንባታ ሥራዎች መነቃቃት የበከሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበትም ዶክተር አሕመዲን አሳስበዋል። የአማራ ክልል መንግሥት የልማት ድርጅት የኾነው የዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ታደሰ ግርማ ኮርፖሬሽኑ ከአማራ ክልል በተጨማሪ በአዲስ አበባ እና በሌሎችም ክልሎች ውስጥ ሥራዎችን እያከናወነ ስለመኾኑ ገልጸዋል። በውል ተረክቦ የሚገነባቸውን ሥራዎች በጥራት እና በአጭር ጊዜ ለማስረከብ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

ኮርፓሬሽኑ ከሀገርም አልፎ በምሥራቅ አፍሪካ የግንባታ ኢንዱስትሪ ላይ ተሳታፊ ለመኾን አልሞ እየሠራ ስለመኾኑም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በቡግና ወረዳ ያለው አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት የታወቀው በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ተከትሎ ነው” አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን
Next article“የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱት በሰላም ነው” በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት