
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሳቢያ 110 ሺህ ወገኖች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ በአካባቢው ያለውን አጠቃላይ ኹኔታ እና እየቀረበ ያለውን ድጋፍ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በክልሉ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ግጭት በዜጎች ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መጠነ ሰፊ ቀውሶችን አስከትሏል፡፡ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የክረምቱን ምቹ የዝናብ ኹኔታ ተከትሎ ምርት እና ምርታማነት በተሻለ ደረጃ ቢገኝም የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ዜጎችን ተጠቃሚ እንዳይኾኑ አድርጓል፡፡
እንደ ሌሎቹ የክልሉ አካባቢዎች ሁሉ በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ የነበረው ምርት እና ምርታማነት የተሻለ እንደነበር ቅድመ ግምገማዎቹ ያሳያሉ ያሉት የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሰርክአዲስ አታሌ ተጨማሪ ድጋፎችን ለማድረግ ግን በአካባቢው የነበረው የፀጥታ ችግር እንቅፋት ኾኖ ቆይቷል ብለዋል፡፡
እናቶች እና ህጻናት ከምግብ ባለፈ የአልሚ ምግብ አቅርቦት ያስፈልጋቸው ነበር፤ በአካባቢው ያንን ድጋፍ የሚያቀርቡ ድርጅቶች መድረስ አለመቻላቸውን አንስተዋል፡፡ “በቡግና ያለው አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት የታወቀው በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ተከትሎ ነው” ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ ለዚህም የችግሩን መስፋት እና አሳሳቢነት ተመልክተው ኀላፊነት የወሰዱ የወረዳው ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌች፣ የሃይማኖት አባቶች እና መላው ማኅበረሰብ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የችግሩን አሳሳቢነት ከደረሰው ቀን ጀምሮ በሦስት ቀናት ውስጥ መረጃዎችን አጠናቅሮ ለፌደራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ማሳወቁን ምክትል ኮሚሽነሯ ተናግረዋል፡፡ መረጃው የደረሰው አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንም ከኮምቦልቻ መጋዘን 1 ሺህ 275 ኩንታል ስንዴ እና 127 ኩንታል አልሚ ምግብ የያዙ መኪኖች በቦታው ደርሰዋል ብለዋል፡፡
በዩኒሴፍ፣ የዓለም ምግብ ድርጅት፣ ቀይ መስቀል፣ ዳሽን ቢራ ፍብሪካ እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በኩል የቀረቡ ድጋፎች ወደ አካባቢው ደርሰው ለተጠቃሚዎች እየተሰራጩ ነው ብለዋል፡፡ በክልሉ ያለው የሰላም እጦት በርካታ ክፍተቶችን ፈጥሯል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሯ አንጻራዊ ሰላም በሚኖርባቸው አካባቢዎች መሰል ክፍተቶች ሊገለጡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በጥናት ላይ የተመሠረተ ምላሽ ለመሥጠት እና ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እየሠራ መኾኑንም ምክትል ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም የጤና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ እና መሠል አቅርቦቶች ለማሟላት ኮሚሽኑ ከአጋር እና ባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅርበት እና በትብብር ይሠራል ብለዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!