የትምህርት ተቋማት የእንስሳት ጤና ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ተጠየቀ።

45

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ለእንስሳት ሐብት ልማት ምቹ እና ጸጋ ያለው አካባቢ ነው። በክልሉ ከሰብል ልማት ቀጥሎ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድርሻ ያለው ዘርፍ እንደኾነም የክልሉ እንስሳት እና ዓሳ ሐብት ልማት ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል። የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሐብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጋሻው ሙጨ (ዶ.ር) የእንስሳት ሐብት በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ከመደገፍ ባለፈ ራሱን ችሎ የኢኮኖሚ አማራጭ በመኾን መተኪያ የሌለው ዘርፍ እንደኾነ ገልጸዋል።

የክልሉ መንግሥት ግብዓት እና ቴክኖሎጅ በማቅረብ፣ በጀት በመመደብ እና የሰው ኃይል በማሟላት የክልሉን እንስሳት ጤና የማሻሻል ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው ኀላፊው የገለጹት። በእያንዳንዱ ቀበሌ የእንስሳት ጤና ተቋማትን በማቋቋም በቅርበት አገልግሎቱን መስጠት ተችሏልም ብለዋል። መንግሥት ከሚሰጠው አገልግሎት ባለፈ የግል ክሊኒኮችም በክልሉ እንዲቋቋሙ በማድረግ ዘርፉን እያገዙ ይገኛሉ ነው ያሉት።

የእንስሳትን ጤና ለመጠበቅ ወረዳዎች ከሚመድቡት በጀት ባለፈ የክልሉ መንግሥትም ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ የእናስሳት ጤና ላይ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በክልሉ ሁለት ቤተ ሙከራዎችን በማቋቋም የእንስሳት በሽታ ቅኝት እና ጥናት በማድረግ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተከናወነ እንደኾነ ተናግረዋል።

በእንስሳት ላይ የሚከሰተውን በሽታ መከላከል ከተቻለ ጥራት ያለው የእንስሳት ተዋጽኦ ወደ ውጭ በመላክ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ እና የወጣቶችን የሥራ ዕድል ማሳደግ ይገባል ብለዋል። በዚህ ዘርፍ መቀንጨርን እና መቀጨጭን መከላከል እንደሚቻልም ገልጸዋል። ይሁንና መንግሥት ከሚሠራው ሥራ ባለፈ የግል፣ የምርምር እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ትኩረት ይሻል ብለዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርና እና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር ጌታቸው አለማየሁ በጣና የኮሪደር ልማት ያለውን የእንስሳት ሐብት ጤና ለማሻሻል የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ትምህርት ቤት ማቋቋም እንዳስፈለገው ገልጸዋል። በቀጣይ የእንስሳት ሆስፒታል ለማቋቋ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

የእንስሳት ሕክምናው ወደ ተሟላ ሥራ ሲገባ በአካባቢው ከእንስሳት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ይቀርፋል ተብሎ ይታሰባል። ቤተ ሙከራዎችን በማደራጀት እና አርሶ አደሩን ተደራሽ ያደረገ ሥራ የሚሠራ ይኾናልም ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል 3 ሺህ ቀበሌዎችን በመንገድ ለማስተሳሰር እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ አስታወቀ።
Next article“በቡግና ወረዳ ያለው አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት የታወቀው በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መምጣቱን ተከትሎ ነው” አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን