በአማራ ክልል 3 ሺህ ቀበሌዎችን በመንገድ ለማስተሳሰር እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ አስታወቀ።

39

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ከአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የ2017 በጀት ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ እንዲኹም የአምስት ወራት የሥራ አፈጻጸምን ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ገምግሟል። የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ፋንቱ ተስፋዬ የመንገድ ቢሮ በ2016 በጀት ዓመት ጥሩ አፈጻጸም እንደነበረው አስታውሰዋል።

ቢሮው ክልሉ ያጋጠመውን የሰላም እጦት ችግር ነው ብሎ ሳይቆም ችግሩን በሥራ ለማለፍ ያደረገው ጥረት መልካም ነበር ነው ያሉት። መንገድ ቢሮ የኅብረተሰቡን የመልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት አድርጓል ያሉት ወይዘሮ ፋንቱ፤ ቢሮው ኅብረተሰቡ የመንገዱ ባለቤት ነኝ ብሎ እንዲጠብቀው አሳታፊ ሥራ አከናውኗል፣ ይህ መልካም ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥልም ይገባል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ከሚመድበው በጀት በተጨማሪ መንገድ ቢሮ ሀብት በማፈላለግ ከአጋር አካላት የተሻለ የመፈጸም አቅም አሳይቷል ብለዋል አፈ ጉባኤዋ። የክልሉ መንገድ ቢሮ ኃላፊ ጋሻው አወቀ(ዶ/ር) ባለፉት አምስት ወራት በመንገድ መሠረተ ልማት ሰፊ ሥራ ተከናውኗል። ይሁንና ከክልሉ ፍላጎት አኳያ ገና ብዙ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ለመንገድ ግንባታ ከ 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ብር መመደቡንም ዶክተር ጋሻው ጠቁመዋል። በሁሉም የመንገድ ዘርፍ የመንገድ ሽፋኑን ወደ 34 ሺህ 572 ኪሎ ሜትር ከፍ ለማድረግ መታቀዱን የተናገሩት ዶክተር ጋሻው በዚህ የመንገድ ግንባታ የቀበሌ ማዕከላትን በመንገድ ለማስተሳሰር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

ስለኾነም በ2017 በጀት ዓመት 3 ሺህ ቀበሌዎችን ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት ሥራው እየተሳለጠ መኾኑን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ 597 የመንገድ እና ድልድይ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ያሉት ቢሮ ኃላፊው ከዚህ ውስጥም 40ዎቹ ድልድዮች ናቸው ብለዋል። በ2017 በጀት ዓመት 17 ሺህ 142 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን ታቅዶ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ 5 ሺህ 64 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።

በግንባታ ሂደቱ የጸጥታ ችግሩ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት አስቸጋሪ ነበር ያሉት ዶክተር ጋሻው የካፒታል ገንዘብም በፍጥነት አለመለቀቁን በውስንነት አንስተዋል። የመንገድ ግንባታዎች የሚያልፉባቸው አካባቢዎች ከሦስተኛ ወገን ነጻ አለመኾንም በችግርነት ቀርቧል። የቋሚ ኮሚቴው አባል በሰጡት አስተያየት በክልሉ በተለይ ተንጠልጣይ ድልድይን በተመለከተ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ተሰርተዋል። ይህ በጎ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ነው ያሉት።

ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግም ኅብረተሰቡን ማሳተፍ ይገባል። የመንገድ እንክብካቤ ላይ ደግሞ ከፍተኛ ጉድለት ይስተዋላልና ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው። መንገዶች በተለያዩ ኹኔታዎች ይታረሳሉ፤ ይፈርሳሉ፤ ይዘጋሉ፤ ስለኾነም የአሠራር ሥርዓት ሊዘረጋለት ግድ ይላል ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው።
ከተጀመሩ ዓመታትን ያስቆጠሩ መንገዶች አሉና ግንባታዎች ቶሎ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲኾኑም ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል ቢሮው የተመደበለትን ከፍተኛ ገንዘብ በርብርብ ሥራ ላይ ማዋል አለበት ነው ያሉት። ጥገና ላይም ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል። ክልሉ ከሚገነባቸው ይልቅ የፌዴራሉ መንግሥት በሚገነባቸው የአስፋልት መንገዶች ላይ ኅብረተሰቡ የጥራት ማጓደል እና የፍጥነት ማነስ ጥያቄዎችን ያነሳል፤ በመኾኑም ጉዳዩን በአግባቡ ፈትሾ እልባት መስጠት ይገባል ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቡግና ወረዳ ለሚገኙ 110 ሺህ ወገኖች አስቸኳይ የሰብዓዊ ደጋፍ እየቀረበ ነው።
Next articleየትምህርት ተቋማት የእንስሳት ጤና ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሠሩ ተጠየቀ።