በቡግና ወረዳ ለሚገኙ 110 ሺህ ወገኖች አስቸኳይ የሰብዓዊ ደጋፍ እየቀረበ ነው።

44

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው 110 ሺህ ወገኖች የምግብ እና አልሚ ምግብ ድጋፍ እየቀረበ መኾኑን የክልሉ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ዛሬ ለብዙኀን መገናኛ ተቋማት በሰጠው መግለጫ የሰብዓዊ ምግብ አቅርቦቱ አፋጣኝ ምላሽ የሚያስፈልገው በመኾኑ የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን፣ የፌደራል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር፣ ረጂ ድርጅቶች እና ግለሰቦች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ርብርብ እየተደረገ ነው ተብሏል።

መግለጫውን የሰጡት የክልሉ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሰርካዲስ አታሌ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት አስቸኳይ የሰብዓዊ ደጋፍ ለሚሹ 110 ሺህ ወገኖች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ስምሪት ተሰጥቷል ብለዋል። የምግብ እና አልሚ ምግብ አቅርቦቱ በአካባቢው ደርሷል ነው ያሉት።

ችግሩ የተፈጠረው በአካባቢው በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመስተጓጎላቸው የተፈጠረ መኾኑን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሯ አሁንም ችግሩ እንዲገለጥ እና ድጋፎች እንዲደርሱ የአካባቢው ማኅበረሰብ የወሰደው ኀላፊነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምስጋናውን አቅርቦ በቀጣይም በጥናት ላይ የተመሠረተ ምላሽ ለመስጠት እየተሠራ ነው ብለዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እስካሁን 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ተሸፍኗል” ግብርና ሚኒስቴር
Next articleበአማራ ክልል 3 ሺህ ቀበሌዎችን በመንገድ ለማስተሳሰር እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ አስታወቀ።