
ደሴ: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የፌዴራል፣ የክልል እና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ዞናዊ የበጋ መስኖ ስንዴ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል። አካባቢያቸው ረግረጋማ ከመኾኑ ጋር በተያያዘ በክረምት ለማምረት አስቸጋሪ እንደነበር እና ለበጋ መስኖ ስንዴ ሥራው በስፋት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት የቃሉ ወረዳ አርሶ አደር አቶ አሕመድ ሀሰን ናቸው።
ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ አድማሴ አበጋዝ የበጋ መስኖ ስንዴ ሥራው አዲስ በመኾኑ ከግብርና ባለሙያዎች በቂ ድጋፍ በማግኘት ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል። ግብዓትም በበቂ ሁኔታ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት 36 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቅቆ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት 254 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን መታቀዱን አስታውሰው እስካሁን 120 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል። ከዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃልም ነው ያሉት።
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ መለስ መኮንን (ዶ.ር) በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ በሀገር አቀፍ ደረጃ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር እንደሚሸፈን መታቀዱን ገልጸው እስካሁን 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
በሁሉም ክልሎች ወደ ተግባር የተገባበት የበጋ መስኖ ስንዴ በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል በትኩረት የሚሠራ ተግባር መኾኑን ያነሱት ሚኒስትር ድኤታው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ስንዴን በመስኖ የመዝራት ተግባር በስፋት ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
ለዚህም በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ለአርሶ አደሮች የማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር አቅርቦት በስፋት እንዲደርሳቸው ተደርጓልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!