ኢትዮጵያ በሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ መሠረተ ቢስ መኾኑን ገለጸች፡፡

41

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ዶሎ በተባለ ከተማ በተፈጠረው ክስተት የኢትዮጵያ ኀይሎችን መክሰሱ ኢትዮጵያን እንዳስቆጣ እና ክሱም ሀሰተኛ መኾኑን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ሀሰተኛ ውንጀላው በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማስተካከል የተጀመረውን ጥረት ለማስተጓጎል የታለመ ነው ብሏል።

ይህም የአፍሪካ ቀንድን ሰላም ለመበጥበጥ የሚፈልጉ እና በቀጣናው ሁልጊዜም ሰላም እንዳይኖር የሚሠሩ የሦስተኛ ወገን አካላት ተግባር መኾኑን መግለጫው አትቷል። በአንካራው ስምምነት ላይ እንደተገለጸው ሁለቱ ሀገራት ለሰላም የሚያደርጉት ቁርጠኝነት እንዳይደናቀፍ ክፍተት መፍጠር የለባቸውም ሲል ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ተመሳሳይ አደጋዎችን ለመከላከል ከሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት የሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር መሥራት እንደሚቀጥልም መግለጫው አትቷል። ኢትዮጵያ በአንካራ ስምምነት መሠረት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማደስ እና ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አጠናክራ ትቀጥላለችም ተብሏል።

የሀገራቱ መሪዎች ለሰላም ያላቸው ቁርጠኝነት የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ቀጣናዊ ትብብርን እንደሚያጠናክርም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አስታውቋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥራት ያለው የምርጥ ዘር ብዜት እንዲሠበሠብ የአማራ ክልል የግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን አሳሰበ።
Next article“እስካሁን 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ተሸፍኗል” ግብርና ሚኒስቴር