ጥራት ያለው የምርጥ ዘር ብዜት እንዲሠበሠብ የአማራ ክልል የግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን አሳሰበ።

29

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2016/2017 በጀት ዓመት ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ጥራት ያለው የዘር ብዜት እንዲሠበሠብ የአማራ ክልል የግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን አሳስቧል፡፡ ወቅቱ የዘር እና የሰብል ምርት መሠብሠቢያ በመኾኑ አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጥራት ያለው እና ደረጃውን የጠበቀ ዘር ለማግኘት መሥራት እንዳለበት ነው የተገለጸው፡፡

ይሁን እንጅ በሠብል መሠብሠብ ወቅት የዘር ጥራት እንዳይጓደል አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባነ ነው የአማራ ክልል የግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን የዘር ብዜት ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጉርሜሳ እጀታ የተናገሩት፡፡ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ የሰብል አይነት ዝርያ ያላቸው ምርጥ ዘሮች በአርሶ አደሮች፣ በዘር አባዥ ድርጅቶች እና በዩኒየኖች በመባዛት ላይ እንደሚገኙም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

ምርጥ ዘሮች ተፈላጊውን የጥራት ደረጃ አሟልተው እንዲመረቱ ለማድረግ ከማሳ ጀምሮ ለተጠቃሚው እስከሚደርስ ድረስ የጥራት ቁጥጥር ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ጥራት ያለው ምርጥ ዘር መሠብሠብ ለአርሶ አደሩ እና በእርሻ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ኢንቨስተሮች ጥብቅና መቆም ማለት ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

አምራቹ ጥራቱ የተረጋገጠ፣ ዝርያው ያልተቀላቀለበት እና ደረጃውን የጠበቀ ዘር እንዲያገኝ በስፋት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህ ደግሞ የክልሉን ምርት እና ምርታማነትን ያሳድጋል ነው ያሉት፡፡ በምርት ዘመኑ በመስክ ሰብል ዘር ብዜት 54 የሚኾኑ ዘር አባዥዎች በዘር ብዜት ሥራ ላይ መሰማራታቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በዚህም በ12 ሺህ 671 ሄክታር መሬት በመስክ ሰብል ዘር ተሸፍኗል፡፡ በዘር ከተሸፈነው ማሳ ወደ 313 ሺህ 295 ኩንታል የምርጥ ዘር ይሠበሠባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ለአሚኮ የተናገሩት፡፡ እስከ አሁን ባለው 37 ሺህ ኩንታል ዘር ተሠብስቦ ወደ መጋዘን መግባት መቻሉን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

አምራቹ ጥራት ያለው ዘር ለማቅረብ እና ከተሰጠው የዘር ግምት ደረጃ እንዳይወርድ፣ እንዳይባክን እና ጥራቱ እንዳይጓደል ጥንቃቄ እንዲደረግ ነው ያሳሰቡት፡፡ ከመሠብሠብ በፊት እና በመሠብሠብ ወቅት የመሠብሠቢያ መሳሪያዎችን ከማጽዳት ጀምሮ ዘር በማበጠር እና በማጓጓዝ በኩል ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየወይዘሮ ስሂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን በቴክኖሎጅ ለማዘመን እየተሠራ ነው፡፡
Next articleኢትዮጵያ በሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መግለጫ መሠረተ ቢስ መኾኑን ገለጸች፡፡