
ደሴ: ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዛሬው የወይዘሮ ስኂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቀደም ሲል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅትም በርካታ ምሁራንን ያፈራ ተቋም ነው።
ኮሌጁ ከቀለሙ ትምህርት ባሻገር ከቅዱስ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመቀጠል በ1956 ዓ.ም ሁለተኛው የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመኾን ዕውቅ ድምጻውያንን በማፍራት በኪነ ጥበቡ ዘርፍ የራሱን ድርሻ አበርክቷል።
ኮሌጁ በቴክኒክ እና ሙያው ዘርፍ ተተኪ ትውልድ ማፍራት ላይ ያለመ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የአማራ ክልል ሥራ እና ሥልጠና ቢሮ መሪዎች፣ የደቡብ ወሎ ዞን እና የደሴ ከተማ የሥራ እና ሥልጠና መምሪያ የሥራ ኀላፊዎች እና ቡድን መሪዎች፣ የወይዘሮ ስኂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የወይዘሮ ስኂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ሰለሞን ይመር ከዓለም ባንክ ድጋፍ የተደረገለት ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንደሚቆይ እና 500 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ስለመኾኑ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ተቋሙን ዲጂታላይዝ ከማድረግ እና አምራች የሰው ኀይል ከመፍጠር አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ነው የኮሌጁ ዲን የተናገሩት።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በርካታ ምሁራን ያፈራውን አንጋፋ ተቋም ዕውቅና ለማሠጠት እና ተሸላሚ ለማድረግ እንደ ከተማ አሥተዳደር ፕሮጀክቱን የመደገፍ እና የመከታተል ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሥራ እና እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው(ዶ.ር) “የወይዘሮ ስኂን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን በቴክኖሎጅ በማዘመን እና ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት የበቁ ተማሪዎች የሚፈሩበት ማድረግ ይገባል” ብለዋል
ዶክተር ስቡህ ገበያው ተቋሙን በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥራት ተወዳዳሪ እና ተሸላሚ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:- ፊኒክስ ሀየሎም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!